
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጦርነት በርካታ ችግሮችን ያሳለፈው ሰሜን ጎንደር ዞን በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶበታል።በዞኑ በ 6 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ከ 86 በላይ ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ ፣የዝናብ እጥረትና የዝናብ መዘግየት ከ452 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለረሃብ እንደተጋለጡ የዞኑ አሥተዳደር መረጃ ያሳያል። በርካታ ነዋሪዎችም ከአካባቢያቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል።
በዞኑ ጠለምት ወረዳ በተከሰተው ድርቅ ከሚኖሩበት ቀበሌ ተፈናቅለው በወረዳው ማዕከል ደጃች ሜዳ ከተማ ተጠልለው ያገኘናቸው ነዋሪዎች በአካባቢያቸው በሚያዚያ ወር የጣለው ዝናብ በግንቦት ወር በመቋረጡ የዘሩት ሰብል መድረቁን ነግረውናል። በዚህ ምክንያት ለረሃብ መጋለጣቸውን ተናግረዋል። የነበራቸውን የቁም እንሰሳትም ግማሹን ሽጠው ሲበሉ ሌሎቹ በድርቁ ምክንያት መሞታቸውን ተናግረዋል።ከዚህ በኋላ ነው ነዋሪዎቹ አካባቢያቸውን ለቀው ለመፈናቀል የተገደዱት።
የደጃች ሜዳ ከተማ ነዋሪዎች ካላቸው እያካፈሉ ሕይወታቸውን እንዳቆዩት የሚናገሩት ተጎጅዎቹ መንግሥት የምግብ ፣የአልባሳት ፣የሕክምና ፣የውኃና መሰል ድጋፎችን በፍጥነት ሊያደርግልን ይገባል ሲሉም ተማጽነዋል።
የጠለምት ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የወረዳው ተወካይ አሥተዳዳሪ ተስፋዬ ወርቅነህ በወረዳው 15 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ ከ 7 ሺህ 200 ሔክታር በላይ ማሳ ከምርት ውጭ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም ከ 62 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለረሃብና ተያያዥ ችግሮች መጋለጣቸውን አብራርተዋል።ከዚህ ውስጥም ሕጻናት ፣ አጥቢ እናቶችና አዛውንቶች ይበልጥ ተጎጅ መኾናቸውን ነግረውናል።
ወረዳው በጠየቀው አስቸኳይ ድጋፍ የክልሉ መንግሥት 600 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። ደባርቅ ዩኒቨርሲቲና ከዞኑ ማኅበረሰብ የተውጣጣ የተለያዬ ድጋፍም ወደ ወረዳው መግባቱን ጠቁመዋል። ኾኖም በወረዳው ካለው ችግር አኳያ የተደረገው ድጋፍ በቂ ባለመኾኑ ተከታታይና የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሣ በዞኑ የተከሰተው ችግር መነሻው 2014 ዓ.ም ነው ይላሉ። በጦርነት ከምርት ውጭ ኾኖ የቆየው አርሶ አደር ድርቅ ዳግም ከምርት ውጭ አድርጎታል። በዞኑ 6 ወረዳዎች በ 86 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ ፣ የዝናብ መዘግየትና እጥረት ከ 452 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የዕለት ደራሽ ምግብ ይፈልጋሉ ብለዋል። በድርቁ በርካታ ቁጥር ያላቸው እንሰሳት መሞታቸውንም ገልጸዋል።
የዞኑ አሥተዳደር ችግሩ በተከሰተ ማግስት ወደ ሥራ መግባቱን ያነሱት አቶ ቢምረው ችግሩን የመለየትና ለሚመለከተው አካል የማድረስ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። በዚህም የክልሉ መንግሥት የ 1 ሺህ 500 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል። ደባርቅ ዩኒቨርሲቲን ፣ የዞኑ ማኅበረሰብንና የተለያዩ አካላትን በማስተባበርም ለተጎጂ ወገኖች ለመድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመነጋገርና ለሚያነሱት ቅድመ ኹኔታ ዋስትና በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርጉ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል። ሰብአዊነት የሚገዳቸው አካላት ሁሉም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንዲደርሱ ምክትል አሥተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!