“የአፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው” ኢጋድ

60

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣናዊ ትስስራቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ሰላምና እድገት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ኢጋድ አስታውቋል።

18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ትናንት ሲካሄድ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር) በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምን ማረጋገጥ የእለት ከእለት ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በቀጣናው የሚገኙ ሀገራት በታሪክና በባሕል የተሳሰሩ እንደመሆናቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን ማጠናከር፣ የተፈጥሮ ሃብትን በጋራ ማልማት እና የድንበር ላይ ንግድን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የድንበር መሬት ጉዳይ አንዱ አጀንዳ መሆኑንም ዋና ጸሐፊው አንስተዋል።

ዋና ጸሐፊው የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ለሀገራቱ ሰላም መስፈን እና የጋራ ትብብር ወሳኝ በመሆኑ “የአፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው” ብለዋል።

በቀጣናው ሀገራት የሚዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በአፍሪካ ቀንድ ድንበር አካባቢዎች ልማትን ለማፋጠን፣ የድንበር መሬትን ለማልማት፣ የጋራ ራዕይ እና የትብብር ስትራቴጂ ለማዘጋጀት እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ የተገለሉ ማኅበረሰቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማስፈን የላቀ ድርሻ አለው ተብሏል።

በሀገራቱ መካከል የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ቁርጠኝነቱ አለ ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፤ ትግበራውን ዕውን ለማድረግ አሳታፊነትን መሠረት ያደረገ ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው ብለዋል።

18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን በአባልነት አቅፎ ይዟል።

ከየካቲት 2015 ዓ.ም ጀምሮም የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት እየመራች መሆኗን የዘገበው ኢፕድ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ በኾነ መሬት የለማ ሰሊጥ እየተሰበሰበ ነው” የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ
Next articleየዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት የቀረቡ ሹመቶችን መርምሮ አጸደቀ።