
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ቆላማ አካባቢዎች በስፋት ከሚመረቱ ምርቶች መካከል አንደኛው ሰሊጥ ነው፡፡ በክልሉ ምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞኖች ደግሞ በስፋት ይመረታል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጤናው ፈንታሁን በምርት ዘመኑ 500 ሺህ 655 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን አቅደው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ 497 ሺህ 825 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አካባቢው የምግብ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችን በማምረት የሚታወቅ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው የሰሊጥ ሰብል እየተሰበሰበ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በምርት ዘመኑ 123 ሺህ 695 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ለመሸፈን አቅደው 160 ሺህ 610 ሄክታር መሬት በሰሊጥ መሸፈናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የሰሊጥ ሽፋኑ ከእቅድ በላይ መኾኑንም ምክትል ኅላፊው ተናግረዋል፡፡ በዘር ከተሸፈነው የሰሊጥ ማሳ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም አመላክተዋል፡፡
ይህ ዜና እስከጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ44 ሺህ ሄክታር በላይ ሰሊጥ መሰብሰቡንም ተናግረዋል፡፡ በአርሶ አደሮች እና በባለሀብቶች ማሳ ላይ ያለው ሰሊጥ እንዲሰበሰብ ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎች በአርሶ አደሮች እና በባለሀብቶች ማሳ በመገኘት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ያለውን ሰብል ለመሰብሰብ በርካታ የሰው ኀይል እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ምክትል ኀላፊው በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የጉልበት ሠራተኞች እንዲገቡና ሰብሉ በወቅቱ እንዲሰበሰብ እያደረጉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዞኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ያለበት በመኾኑ ለሠራተኞች ስጋት የሚኾን ችግር አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡ በየትኛውም የዞኑ አካባቢ ሠራተኞች ተንቀሳቅሰው ለመሥራት የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለም አስታውቀዋል፡፡
ወደ ዞኑ የሚገቡ ሠራተኞች በክልሉ ከሁሉም አካባቢዎች የሚመጡ እንደነበር ያነሱት ምክትል ኀላፊው በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ችግር ወደ አካባቢው ለመምጣት የተቸገሩ ሠራተኞች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡
በዞኑ በእርሻና በአረም ወቅት የገቡ ሠራተኞች ባሉበት ቆይተው የምርት መሰብሰቡን ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከጎንደር ወደ ገንዳውኃ እና በምዕራብ አርማጭሆ ያለው መስመር ለትራንስፖርት ክፍት መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው ሠራተኞች ወደ አካባቢው መምጣት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ያለውን የሰሊጥ ምርት ለመሰብሰብ 1 ሚሊዮን ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉም አስታውቀዋል፡፡ የሰሊጥ ምርት ወቅትን የሚጠይቅ እና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከዘነበ ጉዳት እንዳይደርስ ርብርብ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ወቅቱን ጠብቆ ለመሰብሰብ በርካታ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት፡፡
በቀን ሠራተኞች እጦት ምክንያት እስካሁን በምርታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው አርሶ አደሮች እና ባለሃብቶች አለመኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ካለው ሰብል አንጻር ግን አሁን ከገባው ሠራተኛ በላይ በርካታ ሠራተኞችን እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!