
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የተከሰተውን የመንገድ ብልሽት የመጠገን ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ መንገድ ቢሮው ገልጿል፡፡
እንደ መንገድ ቢሮ ገለጻ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች በተከሰተው የመንገድ ብልሽት ምክንያት ኅብረተሰቡ ለእንግልት እና ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ ይገኛል፡፡ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውም ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል ተብሏል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍም ቢሮው መንገዶችን በአፋጣኝ ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እያደረገ ስለመኾኑ ነው የሚገልጸው፡፡
በአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የመንገድ አውታር ኮንትራት አሥተዳደር ዳይሬክተር መሰለች ብናልፈው ለአሚኮ እንዳሉት ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶች ለመጠገን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በመንገድ ብልሽት ምክንያት ለችግሮች እየተዳረገ ያለውን የክልሉን ሕዝብ ለመታደግ መንገዶችን በአፋጣኝ ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በዚህ ዓመትም ወደ 4ሺህ 500 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ስለመኾኑ ነው ወይዘሮ መሰለች ያብራሩት፡፡
በ204 የመንገድ መስመሮች ላይ የሚሠራውን የመንገድ ጥገና ሥራ ለማካሄድ ክልሉን በ6 ቀጣና ከፍሎ ሥራው በጥራት እንዲሠራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ዳይሬክተሯ ነግረውናል፡፡
ቢሮው ከመደበኛ የመንገድ ጥገና ሥራ ባሻገር በድንገተኛ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶችም የጥገና ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ባለው የሰላም ሁኔታ ግን ሥራዎችን በታሰበው ፍጥነት እና ጥራት ለማካሄድ እንቅፋት እየኾነ እንደኾነ የተናገሩት ዳይሬክተሯ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!