
ባሕር ዳር፡- ጥር 22/2012ዓ.ም (አብመድ) የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ክብረ በዓል ከዋዜማው ጀምሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡
የሰባት ቤት አገው 80ኛ ዓመት የፈረሰኞች ክብር በዓል ነገ በእንጅባራ ከተማ ይከበራል። ዛሬ ደግሞ የበዓሉ አካል የሆነው የቋንቋ፣ የታሪክ እና የባህል ሲምፖዚየም ተካሂዷል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን በሲምፖዚዬሙ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ሕዝብ በቋንቋ፣ በባህል፣ በታሪክ እና በአኗኗር የማይለያይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዊ ሕዝብም የሌሎችን ማንነት በማክበር የራሱን ባህል፣ ወግና ማንነት ለዘመናት ጠብቆ የኖረ መሆኑንም ነው የተናገሩት። የፈረሰኞች በዓልም ለዚህ ማሳያ ከሆኑ አብነቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ መደረጉ ቋንቋውን ለማሳደግ ያበረከተው አስተዋጽዖ የጎላ እንደሆነም በውይይቱ ቀርቧል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) የአዊ ሕዝብ አካባቢውንና ስነ ምህዳሩን ከልምዱ ጋር አስተሳስሮ የሚኖር ሕዝብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ተጠብቆ የኖረ ሃገር በቀል እውቀትም በስርዓተ ትምህርት ተቀርፆ መሰጠት እንዳለበት ነው ሀሳብ ያቀረቡት፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራች አቶ ኦባንግ ሜቶ ስለሰላም ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ ‹‹የቀደሙት አባቶች በዘር፣ በቋንቋ ሳይከፋፋሉ ሀገር ጠብቀው እንዳስረከቡት የዛሬው ትውልድም በኢትዮጵያዊነት ጽኑ አለት ላይ በመቆም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል›› ብለዋል፡፡
የሰባት ቤት አገው 80ኛ ዓመት የፈረሰኞች ክብር በዓል ነገ ጥር 23/2012 ዓ.ም በፈረስ ጉግስ ውድድር እና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው