“ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር

43

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት በሰሜን ሸዋ ዞን እና በደብረ ብርሃን ከተማ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

77 ሺህ ተፈናቃዮች በሰሜን ሸዋ ዞን እና በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥም 22 ሺህ የሚሆኑት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ናቸው። እስካሁንም ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ወደ ዞኑ የሚያቀኑ ወገኖች መኖራቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የሰላም እጦትን ተከትሎ በቂ ግብዓት አለመቅረብ፣ በዝናብ እጥረት፣ በግሪሳ ወፍ፣ በጢንዚዛ እና በዋግ በሽታ ክስተት ምክንያት በ19 ወረዳዎች ከ56 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከመኸር ምርት ውጪ መሆኑንም ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል። ይህም ከ285 ሺህ በላይ ዜጎችን ለችግር ተጋላጭ አድርጓል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አበባው መሰለ አሁን ላይ ተፈናቃዮች አፋጣኝ የምግብ ድጋፍ ካላገኙ ችግሩ የባሰ እንደሚሆን አመላክተዋል።

በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የሰላም መደፍረስ ለሥራው አዳጋች ቢሆንም ከፌዴራል ማእከላዊ መጋዘን እስከ ደብረ ብርሃን ድረስ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማጓጓዝ በአንጻራዊነት ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩም ጠቅሰዋል።

ይህንን ችግር በመቅረፍ ሂደቱ የረጂ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው። በየዘርፉ እየተሳተፉ ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ስለመሆኑ በደብረብርሃን ከተማ በተካሄደ የውይይት መድረክ ተነስቷል። በውይይቱ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ሀሳብ ተንሸራሽሯል። ልዩ ልዩ የረጂ ድርጅቶች በየዘርፉ ተሳትፎ እያደረጉ ቢሆንም ካለው ችግር አንጻር በቂ አለመሆኑን ነው አሚኮ ያነጋገራቸው የድርጅቱ ተወካዮች የገለጹት።

አቶ አበባው እንዳሉት ደግሞ አንዳንድ ድርጅቶች በወሰዱት ስምምነት መሠረት እየሠሩ አለመሆኑ ተረጋግጧል። ይህ ችግር እንዲፈታ ለማድረግ አሠራር መዘርጋቱን በመግለጽም በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

በንጹሃን መፈናቀል ምክንያት የሚደርሰውን ሰቆቃ ለማስቀረት በቀዳሚነት መፈናቀልን ማስቆም ይገባል ያሉት አቶ አበባው ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋም ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዩኒቨርሲቲው ሥም የተሰራጨው የተማሪዎች ጥሪ ደብዳቤ ሐሰተኛ እና የተቀነባበረ ነው” ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
Next article“በክልሉ ከ4ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው” የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ