“በዩኒቨርሲቲው ሥም የተሰራጨው የተማሪዎች ጥሪ ደብዳቤ ሐሰተኛ እና የተቀነባበረ ነው” ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

119

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እንደ ኢትዮጵያ አሁናዊ እና ነባራዊ ኹኔታ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ፈታኝ እየኾነ መጥቷል፡፡ በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያውን ክስተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሕዝብን እና ሀገርን የሚጎዱ ሐሰተኛ መረጃዎች በስፋት ይሰራጫሉ፡፡

መስከረም 19/2016 ዓ.ም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራር እና አልሙናይ ማኔጅመንት ያወጣው በማስመሰል የተሳሳተ የተማሪዎች ጥሪ ደብዳቤ በማኅበራዊ ሚዲያው ተሰራጭቷል ያሉን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ግርማው አሸብር ናቸው፡፡

አቶ ግርማው የተሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ “መደበኛ ተማሪዎች ጥቅምት 4 እና 5/2016 ዓ.ም እንዲገቡ እና የማታ እና የሪሚዲያል ተማሪዎችን ጥሪ በቅርቡ እንገልጻለን” የሚል ነበር ብለዋል፡፡

የተሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ የዩኒቨርሲቲውን ማሕተም እና አርማ ቆርጦ በመለጠፍ እጅግ ተቀራራቢ እና ተመሳሳይ በኾነ መንገድ የተቀነባበረ ነው ተብሏል፡፡ “በዩኒቨርሲቲው ስም የተሰራጨው የተማሪዎች ጥሪ ደብዳቤ ሐሰተኛ እና በውሸት የተቀነባበረ ነው” ያሉት አቶ ግርማው በተማሪዎቻችን እና በተማሪ ወላጆች ላይ ጫና የፈጠረ ነበር ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች በተለይም በይነ መረብ ተደራሽ በኾነባቸው አካባቢዎች ሐሰተኛ መረጃው ተደራሽ ኾኗል፡፡ ተማሪዎቹ መምህራንን እና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ስልክ በመደወል ጠይቀዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው የችግሩን አሳሳቢነት በማየት መረጃ ማስተላለፉንም ነግረውናል፡፡

ዩኒቨርሲቲው “ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ” በሚል ሥም በከፈተው እና ከ200 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገጹ ላይ ትክክለኛ መረጃዎችን እንደሚያጋራም ተናግረዋል። የተሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ ትክክል አለመኾኑንም በዚሁ የዩኒቨርሲቲው ገጽ አጋርተናል ብለዋል፡፡

አቶ ግርማው ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ጥሪን በመደበኛ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት እና በዩኒቨርሲቲው የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎች በቀጣይ ያሳውቃል ብለዋል፡፡ ጥሪ እስከሚያስተላልፍበት ጊዜ ድረስ ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች በትዕግስት እንዲጠብቁ እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን በጥንቃቄ እንዲከታተሉም ጠይቀዋል፡፡

የተሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መኾኑን ተከታትለው ለዘገቡ የብዙሃን መገናኛ እና የእውነት ማጣራት ተቋማት ዩኒቨርሲቲው ምሥጋናውን ያቀርባል ብለዋል አቶ ግርማው፡፡

ዘጋቢ:- በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የኮሌራ ወረርሽኝ ስርጭት እየሰፋ መምጣቱን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
Next article“ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር