በአማራ ክልል የኮሌራ ወረርሽኝ ስርጭት እየሰፋ መምጣቱን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

72

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ከሐምሌ 8/2015 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብ ጎንደር ቋራ ወረዳ የተቀሰቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ አሁን ላይ 31 ወረዳዎችን አዳርሷል።

እስካሁን ባለው መረጃም መሠረትም በወረርሽኙ 4 ሺህ 84 ሰዎች ተጠቅተዋል። የ76 ሰዎችን ሕይዎት ደግሞ ነጥቋል ነው የተባለው።

በቋራ ወረዳ የተነሳው የኮሌራ ወረርሽኝ ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ደራ፣ ምሥራቅ ደንቢያ፣ አለፋ፣ ምዕራብ በለሳ፣ ጎንደር ከተማ፣ ጃንአሞራ እና በመሳሰሉ የክልሉ ምዕራባዊ አካባቢዎች እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጿል።

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አብርሃም አምሳሉ ካለፉት ሦስት ቀናት ጀምሮ ደግሞ በደብረ ብርሃን ከተማ በሽታው ተከስቷል ብለዋል።

በሽታው ከተከሰተባቸው 31 ወረዳዎች ውስጥ በክትባት አቅርቦት እጥረት ምክንያት ሥርጭቱ ጎልቶ በታየባቸው ሰባት ወረዳዎች እና በሁለት ከተማ አሥተዳደሮች ብቻ ክትባቱ እንዲሰጥ ተደርጓል። በእነዚህ አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የክትባቱ ተደራሽ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።

ክትባቱን በቀጣይ ዙር ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠሩ መኾኑም ተነስቷል።

የክትባት አቅርቦቱ እንደደረሰ ከዚህ በፊት ተደራሽ ባልኾነባቸው እና ተጋላጭ በኾኑ የፍልሰተኞች መጠለያ ጣብያዎች እና የልማት ቀጣናዎች ላይ ለመሥጠት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ማኅበረሰቡ ለበሽታው አጋላጭ የኾኑ የተበከለ ውኃን በማከም፣ ምግብን ደግሞ አብስሎ እንዲጠቀም እና የአካባቢና የግል ንጽህናን በአግባቡ መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የመንግሥት ተቋማትም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአዉሮፖ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጋቸዉን የትብብር ሥራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል” የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር
Next article“በዩኒቨርሲቲው ሥም የተሰራጨው የተማሪዎች ጥሪ ደብዳቤ ሐሰተኛ እና የተቀነባበረ ነው” ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ