
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአዉሮፖ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጋቸዉን የትብብር ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር ተወያይተዋል።
በዉይይታቸዉም የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር መኾኑን ተናግረዋል ሚኒስትሯ። ኅብረቱ እስካሁን ላደረጋቸው የትብብር ተግባራትም ምሥጋና አቅርበዋል። የዚሁ ትብብር አካል የኾነው የ650 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ማዕቀፍ ይፋ በመኾኑም ሚኒስትሯ ምሥጋና ችረዋል።
የመካከለኛ ዘመን የሦስት ዓመቱን የኢንቨስትመንት እቅድ እንዲሁም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለትን ይዘቶች በተመለከተ ዶክተር ፍጹም ገለጻ አድርገዋል። ኅብረቱም የመንግሥትና የሕዝብን ትኩረቶች በመረዳት ትብብሮችን እንዲያደርግ እንደሚያስችለው ማብራራታቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ኅብረቱ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ግብርና ሥራዎች እና ብዝሐ ሕይወት ጥበቃ ከኢትዮጵያ ጋር ይሠራል ብለዋል። በአረንጓዴ ልማት፣ አካባቢ ጥበቃና ታዳሽ ኃይል ልማት፣ ለሰው ኃይል ልማት ፣ በጤና ፣ በመልካም አሥተዳደር፣ ሰላም ግንባታና የዴሞክራሲ ልማት ሥራዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!