የሰላም እጦት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት ፈታኝ እንዳደረገበት የንግድ እና ገብያ ልማት ቢሮ አስታወቀ

73

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ እያሻቀበ መጥቷል፡፡ በየቀኑ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ እየጨመረ የኅብረተሰቡን ኑሮ አዳጋች አድርጎታል፡፡

በየደረጃው ያሉ ተቋማት ይህንን ችግር ለመፍታት ስለምን ተሳናቸው? አሚኮ ከዚህ በፊት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ በመንግሥት በኩል የቆዩ አሠራሮችን በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመፈተሽ ጥረት አድርጓል፡፡

የኑሮ ውድነቱን ችግር ለመፍታት በመንግሥት ከተቀመጡ አሠራሮች ውስጥ አንዱ የሸማች ማኅበራትን በማደራጀት የፍጆታ እቃዎችን እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው፡፡

ማኅበራቱ የኑሮ ውድነቱን በተወሰነ ደረጃ ማስታገስ ቢችሉም አሁን ላይ ግን ባለው የሰላም እጦት ምክንያት ተንቀሳቅሰው እና ከአምራቹ ማኅበረሰብ ገዝተው ማቅረብ አልቻልንም ይላሉ፡፡

አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ በባሕር ዳር የሚገኙ የጣና፣ የጥምረት እና የግዮን ኅብረት ሥራ ማኅበራት በአካባቢያቸው የሚገኙ ምርቶችን ለተጠቃሚው እያቀረቡ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ከአምራቹ በቀጥታ ምርት ገዝተው ለተጠቃሚው ለማቅረብ የሰላሙ እጦቱ ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ንግድ እና ገብያ ልማት ቢሮ በበኩሉ “አስተማማኝ ሰላም አለመረጋገጡ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ምክንያት ኾኗል” ብሏል።

ቢሮው የሰላም እጦት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት ፈታኝ እንዳደረገበት ነው የገለጸው፡፡

የንግድ እና ገብያ ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቢታ ገበያው እንዳሉት አሁን ላይ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን አገልግሎት ለማስቀጠል ባለሙያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ ነው የገለጹት፡፡

አሁን ላይ በክልሉ ያለውን የኑሮ ውድነት እያባባሰው ያለው ምርት ከአንዱ ወደ ሌላው አካባቢ በነጻነት መዘዋወር ባለመቻሉ ነው ሲሉም የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አስረድተዋል፡፡

ቢሮው በተቻለ መጠንም ቢኾን ያለውን ችግር ለማቃለል ክልሉን በአራት ቀጣና ከፍሎ እና ስምሪት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነም ነው የነገሩን፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው የሰላም ኹኔታው ሲሻሻል የኑሮ ውድነቱም ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ሕጋዊ መስመሩን ተከትሎ እንዲቀጥል ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ340 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዳግም ሰብል እንደሚለማ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next article“የአዉሮፖ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጋቸዉን የትብብር ሥራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል” የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር