
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በቀሪ እርጥበት ከ340 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከአምስት ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ እንዬ አሠፋ በ2015/16 የመኸር እርሻ ቀድመው የሚደርሱ ሰብሎችን በማንሳት በቀሪ እርጥበት 341 ሺህ 247 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በዳግም ሰብል ገብስ፣ ጓያ፣ ሽንብራ፣ ስንዴ፣ አብሽ፣ ምስር እና አጃ በሥፋት የሚለሙ ሰብሎች መኾናቸውንም ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡
በዳግም ሰብል እርሻ ሥራው ላይ ከ500 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም ወይዘሮ እንዬ ጠቁመዋል፡፡
ማሣን በድግግሞሽ ማለስለስ እና የመኸሩ ዝናብ በበቂ መጠን መገኘት የተሻለ ምርት ለማምረት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
በቀሪ እርጥበት ዳግም ማምረት የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት ለማግኘት ቀሪ እርጥበቱ ሳያልፍ ማሣቸውን ማለስለስ እና መዝራት እንዳለባቸው ባለሙያዋ አሳስበዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም በቀሪ እርጥበት ከአምስት ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡንም ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!