
ባሕር ዳር፡- ጥር 22/2012ዓ.ም (አብመድ) በአካባቢው የፈረሰውን የመንግሥት መዋቅር መመለሱን የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ምእራብ ዕዝ አስታውቋል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ ለሦስት ቀናት የዘገባ ቅኝት አድርጓል፡፡ ደምቢ ዶሎ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ሌሎች ሰዎች እገታ ጋር በተያያዘ ስሙ በዚህ ወቅት በተደጋጋሚ የሚነሳ አካባቢ ነው፡፡ በቆይታውም ከምልከታ ባሻገር ዩኒቨርሲቲውን እና በአካባቢው ለጸጥታ ሥራ የተሠማራውን የምዕራብ ዕዝ አዛዥ አነጋግሯል፡፡
የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ምእራብ ዕዝ 12ኛ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ገዳ በዳዳ ሰራዊቱ የአካባቢውን የፈረሰ የመንግስት መዋቅር መመለሱን ተናግረዋል፡፡ አሁን ፀጥታውን በተሻለ ሁኔታ መቆጣጠር እንደተቻለም ነው ኮሎኔል ገዳ የተናገሩት፡፡
የመንግሥት መዋቅሩን ወደተሻለ ደረጃ ይመልሱት እንጂ አሁንም በአካባቢው እገታ እና ሰዎችን አፍኖ የማቆት እንቅስቃሴ መኖሩን፣ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩትም የዚሁ ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
የአጋቾችን ማንነት በተመለከተ እውቅና ስለመኖሩ የተጠየቁት የዕዙ አዛዝ ለአብመድ እንደገለጹትም ከአጋቾቹ ጀርባ ‹‹የሸኔ አባል›› እንደሚኖር ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ከዚህ ያለፈ መረጃ ግን እንደሌላቸው ነው የተናገሩት፡፡ የታገቱ ተማሪዎችን በሚመለከት ፍንጮች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ደግሞ ታግተዋል ከተባሉት 17 ሰዎች ውስጥ 12ቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደሆኑ ማረጋገጡን ነው የገለጸው፡፡ ሪፖርት ከቀረበባቸው በተጨማሪ የት እንደደረሱ የማይታወቁ ሌላ ሁለት ተማሪዎች መኖራቸውንም አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት እስካሁን የት እና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የማይታወቁት የዩኒቨርቲው ተማሪዎች 14 ይሆናሉ፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ በሰጡት የጋራ መግለጫ ደግሞ 14 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ሌሎች አምስት ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 19 ሰዎች የት እንዳሉ፤ ማን፣ እንዴትና ለምን እንዳገታቸው ምርመራ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም አንድ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
‹ጉዳት ደርሶባቸዋል› የተባለውን መረጃ በተመለከተ ግን እስካሁን በፖሊስ የተደረሰበት መረጃ እንደሌለ፣ ጉዳዩም ውስብስብና ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ በአካባቢው ኢንተርኔትና ሥልክ መቋረጡን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ እስካሁን 800 የደምቢዶሎ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው አንዳቋረጡ አልተመለሱም፡፡
በቄለም ወለጋ ዞን ባለሃብቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች በአካባቢው እየታገቱ የቆዩ ስለመሆናቸው አብመድ በአካባቢው በነበረው ቆይታ ታዝቧል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን