መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ ቅኝት በበዓል ዋዜማ

390

መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ ቅኝት በበዓል ዋዜማ

የየትኛው ምርት ዋጋ ቀነሰ? የየትኛውስ ጨመረ?

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 27/2011ዓ.ም (አብመድ) በዓላትን ምክንያት በማድረግ በተለያዪ አካባቢዎች የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ምን እየተሰራ እንደሆነ የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ የሸማቾች ጥበቃ ክፍልን አነጋግረናል፤ የባህር ዳር ከበያንም ቃኝተናል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞንና እና በአዊ ብሄረሰብ አሥተዳደር አገልግሎት ላይ እየዋለ ካለው ተጨማሪ 888 ሺህ 650 ሊትር ቀሪ ክምችት የምግብ ዘይት መኖሩን መረጃ አግኝተናል፡፡ በባህር ዳር ደግሞ 1 ሚሊዮን 212 ሺህ 531 ሊትር ዘይት በቀሪ ክምችት ላይ ይገኛል፡፡

በማንኛውም ክስተት ወይም ጊዜ በገበያ እጥረት ቢከሰት ክምችቱ ለመጠባበቂያነት ያገለግላል፡፡ ሆኖም ዘይት በተረጋጋ ሁኔታ እየተሰራጨ ነው እንበል እንጂ ሙሉ በሙሉ ፍላጎትን የሚያረካ ለመሆኑን የክልሉ ሸማቾች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ሙሃባው ሙላት ነግረውናል፡፡

በሌላ በኩል ከፍተኛ የስኳር ፍላጎት ቢኖርም እጥረቱ አሳሳቢ መሆኑ ተገልጧል፡፡ በክልሉ የስኳር ኮታ ከህዝብ ብዛቱ ጋር አይመጣጠንም ነው ያሉት አቶ ሙሃባው፡፡ ወርሃዊ ድርሻውም 72 ሺህ ኩንታል ብቻ ነው፡፡ 
የስንዴ ዱቄት በአቅርቦት ችግር ምክንያት በሰፊው እየተሰራጨ አይደለም፡፡ ለአብነት በምዕራብ ጎጃም ዞን በሶስት ወይም በአራት ወራት ልዩነት ነው የሚደርሰው፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን በአማካይ የዘይት ዋጋ በሊትር 25 ብር፣ ስኳር በኪሎ 19 ብር፣ ስንዴ ዱቄት በኪሎ 11 ብር እየተሸጡ ነው ብሏል ቢሮው፡፡ ደቡብ ወሎ ላይ ደግሞ የአቅርቦት እና የዋጋ ችግር ባይነሳም ገዢው በሚፈልገው መጠን እያገኘ አይደለም፡፡

የሌሎች ምርቶችን ዋጋ ስንመለከት ደግሞ ነጭ ሽንኩርት በኪሎ ከነበረበት 32.60 ወደ 35.50 ብር ከፍ ብሏል፣ ቀይ ሽንኩርት በፊት ከነበረበት 19.50 ወደ 17.50 ብር በመሆን የ1.80 አካባቢ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ቅቤ ህዳር ወር ላይ በኪሎ 213 ብር ነበር የተሸጠው፡፡ ታህሳስ ወር ላይ ደግሞ የሶስት ብር ጭማሪ አሳይቶ 216 ብር ሆኗል፡፡ በርበሬ በኪሎ 66 ብር ሲሸጥ ቆይቶ ወደ 68 ብር አሻቅቧል፡፡

የጥራጥሬ ምርቶች አጠቃላይ ዋጋቸው አድጓል፡፡ በተለይ ምስር ህዳር ላይ የነበረውን ዋጋ ከታህሳስ ወር ጋር ስናነጻጽረው በኪሎ በ2.50 ብር ያህል አድጓል፡፡

ስንዴና ጤፍ ሰፊ የሚባል የዋጋ ጭማሪ እንዳላሳዩ ነው የተጠቀሰው፡፡ ቲማቲም ከነበረበት 16 ብር በኪሎ ወደ 14 ብር ቀንሷል፡፡

በምልከታችን እና ከሸማቾች አስተያየት እንደተረዳነውም የምስር እና የበርበሬ ዋጋ ጭማሪ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ አቅርቦቱ ግን በስፋት እንደሚገኝ አስተውለናል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Next articleON AIR