
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እንዲሁም በምክክሩም ንቁ ተሳታፊ ለመኾን ዝግጅት ማድረጉን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሪዎች ጋር የኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያከናወናቸው ሥራዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በመድረኩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ ኮሚሽኑ የተሳካ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ እስካሁን ያከናወናቸው ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
በተለይም ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና ሁሉን አሳታፊ ለማድረግ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተሄደበት ርቀትና አጠቃላይ ጥረቶች የሚደነቁ መኾናቸውን ነው ያነሱት።
በቀጣይም “ከማን ምን ይጠበቃል” የሚለውን በመለየትና ቀሪ ሥራዎችን በተሳካ መልኩ ለማከናወን ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያየ መሆኑን በገለጻው ለመረዳት ማቻላቸውን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የብልጽግና ጉዞዋን ለማፋጠን እንደሚያስችል ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ ከብልጽግና ፓርቲ አባላት ጋር በተካሄደ ሰፊ ውይይት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ገዥ ፓርቲ የሚጠበቅበትን ድጋፍ በየደረጃው በሚገኙ የፓርቲ መሪዎች በኩል እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፓርቲው ለኮሚሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡
ኢዜአ እንደዘገበው ፓርቲው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ ለመኾንና ሀገራዊ ምክክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የምክክር ውጤቱን ገቢራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!