የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከመስከረም 28 እስከ 30/2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

61

ባሕር ዳር: መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው የሆነው ብሄራዊ የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከመስከረም 28 እስከ 30 /2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በግል እና በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በድህረ ምረቃ መርሐ ግብር ለመማር የሚገቡ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተናው በሀገሪቱ ባሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል ብሏል ሚኒስቴሩ።

ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች ከመስከረም 21 እስከ 25/2016 ዓ.ም ድረስ በተዘጋጀው https:/portal.aau.edu.et ድህረ ገፅ ላይ የዩኒቨርሲቲዎች የቴሌ ብር አካውንትና ሌሎች መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉ ሲኾን ለአገልግሎቱ 1 ሺህ ብር በመክፈል መመዝገብ ይቻላል ተብሏል።

በቴክኖሎጂ ታግዞ በሚሰጠው ፈተና የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ለመውሰድ በግልም ይሁን በመንግሥት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች በፍጥነት ማመልከት ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።

የፍተና ይዘቶቹ ለሁሉም ተመዝጋቢዎች ተመሳሳይ መኾናቸውን የገለጹት የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ተወካይ ሚኒስትር ዴኤታው ሰለሞን አብርሀ (ዶ.ር) ችግር ፈቺ ፣ በጥልቀት ማሰብና ማሰላሰል እንዲሁም የሳይንስ ፅንሰ ሃሳቦች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተዘጋጀው ፈተና ላይ የዩኒቨርሲቲዎች የኢንተርኔት (ዋይ ፋይ) አገልግሎት ክፍት ይደረጋል ነው ያሉት። አሁን ላይ ለምዝገባ በስልካቸው ላይ ባለ የቴሌ ብር ሱፐር አፕ ያለ ኢንተርኔት መመዝገብ ይችላሉ ነው የተባለው።

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በክልሉ ወቅታዊ ኹኔታዎች ላይ እየተወያዩ ነው።
Next article“ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል” የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ