“በአማራ ክልል የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ጀምረናል።” ግብርና ሚኒስቴር

87

ባሕር ዳር: መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሀገር በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች የግሪሳ ወፍ ተከስቶ በማሳ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ክስተቱን ተከትሎ የግብርና ሚኒስቴር በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በላይ መንግሥቴ በአማራ ክልል የተፈጠረው የግሪሳ ወፍ ክስተት በዚህ ወቅት የተለመደ አልነበረም ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ተሞክሮ በመነሳት ምናልባትም ክስተቱ ጥቅምት መጨረሻ አካባቢ ይፈጠራል የሚል ስጋት ነበር ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በክልሉ የተፈጠረው የግሪሳ ወፍ ስርጭትን ለመግታት ግብርና ሚኒስቴር በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ጀምሯል ብለዋል፡፡

አሁን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጠረው የግሪሳ ወፍ ስርጭት የኬሚካል ርጭቱ በአንድ አውሮፕላን ብቻ እየተፈጸመ እንደኾነ ነው ያስረዱት፡፡ በቅርብ ጊዜያት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡

የኬሚካል ርጭቱ በክልሉ ካለው ነባራዊ ኹኔታ አንጻር በጥንቃቄ እና በጥናት እየታየ የሚፈጸም ነው ተብሏል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የኬሚካል ርጭቱ በስፋት እንደሚካሄድ አቶ በላይ ተናግረዋል፡፡

መሪ ሥራ አስፈጻሚው ከኬሚካል ርጭቱ በተጨማሪ አርሶ አደሩ በማሳው ላይ የሚያደርገውን ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በየማሳው ማማ ሠርቶ መጠበቅ፣ የግሪሳ ወፍ መፈልፈያ አካባቢዎች ላይ የወፎችን ጎጆ ማፍረስ እና ባሕላዊ መከላከያ መንገዶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭቱ መስከረም 21/2016 ዓ.ም መጀመሩን ነግረውናል፡፡ በክልሉ ምሥራቅ አማራ አካባቢ የተጀመረው የኬሚካል ርጭት በአፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ሁሉ በመጭዎቹ ቀናት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለአማራ ሕዝብ የሚያስብ ሁሉ የአማራ ሕዝብ እንዳይጎዳ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ አለበት።” ዲያቆን ተስፋው ባታብል
Next articleየአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በክልሉ ወቅታዊ ኹኔታዎች ላይ እየተወያዩ ነው።