
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በወቅቱ ሁለት ታላላቅ ፈተናዎች አሉ፡፡ የሰላም እጦት እና የዝናብ እጥረት፡፡ የሰላም እጦቱ ለዜጎች ሞት ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ወድመት አስከትሏል፡፡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት እና ወደ ሕክምና ተቋማት መንቀሳቀስ የማይችሉ በርካቶች ናቸው፡፡
የሰላም እጦቱ ነጋዴዎች እንዳይነግዱ፣ አርሶ አደሮች ተረጋግተው እንዳያርሱ አድርጓቸዋል፡፡ ተማሪዎች በወቅቱ እንዳይመዘገቡ፣ በወቅቱም ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ እና ተወዳዳሪ እንዳይኾኑም አዘግይቷቸዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን የሚስቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ጎብኚዎችን ናፍቀዋል፣ በቱሪዝም ላይ ገቢያቸው የተመሠረቱ ወገኖች ያለ ሥራ ተቀምጠዋል፡፡
የሰላም እጦቱ ባለሀብቶች በክልሉ መዋለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱም አድርጓቸዋል፡፡ ተስፋ የተጣለባቸው ታላላቅ ፕሮጄክቶችም ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ የሰላም እጦቱ በክልሉ እያሻቀበ የመጣውን የኑሮ ውድነትም አባብሶታል፡፡ ምርት ከቦታ ቦታ ባለመንቀሳቀሱ፣ አምራቹም ተረጋግቶ ምርቱን ወደ ገቢያ እንዳያቀርብ አድርጎታል፡፡
ሌላኛው የአማራ ክልል ወቅታዊ ፈተና የዝናብ እጥረትና ያን ተከትሎ የመጣው የወገኖች መጎዳት ነው፡፡ በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የዝናብ እጥረት ተከስቷል፡፡ በተከሰተው የዝናብ እጥረት ሳቢያም በርካታ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ይሻሉ፡፡ የእንስሳት መኖም አስቸጋሪ ኾኗል፡፡ እነዚህ ሁለት ታላላቅ የወቅቱ ፈተናዎች ክልሉን ጎድተውታል፡፡ መፍትሔው ቅርብ እና አስቸኳይ ካልኾነም ከዚህ የበለጠ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ በተፈጠሩ ችግሮች ተፈናቅለው ድጋፍ የሚሹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖች አሉ ብለዋል፡፡
በክልሉ በዝናብ እጥረት ምክንያት በሰሜን ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአንዳንድ ወረዳዎች የዝናብ እጥረት ተከስቷል፡፡ በተከዜ ተፋሰስ ባሉ ወረዳዎች ደግሞ የዝናብ እጥረቱ ከፍ ያለ ችግር አለበት፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ደግሞ በግሪሳ ወፍ ወረራ ምክንያት ችግር ተከስቷል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በክልሉ በዝናብ እጥረት ምክንያት አንድ ሚሊዮን ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ይሻሉ፡፡
ረጅ ድርጅቶች ከግንቦት 2015 ዓ.ም ጀምሮ እርዳታ ማቆማቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ ከዚያ ጀምሮ ያለውን የክልሉ መንግሥት ለመሸፈን በጀት መድቦ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የክልሉ መንግሥት እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ድጋፍ መላኩንም አንስተዋል፡፡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ግን በቂ አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም በመጠለያ ለሚኖሩ ወገኖች ድጋፍ እያቀረበ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የተላከው ድጋፍ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ሊደርስ አለመቻሉንም ገልጸዋል፡፡ በአካባቢውም ድጋፍ እየተሰበሰበ እንዲደርስ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ችግሮችን ገምግሞ የጋራ እቅዶችን ማውጣቱንም ገልጸዋል፡፡ ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የገጠመው ችግር ሁሉን አቀፍ ርብርብ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡ የተሻሉ አርሶ አደሮች፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ወገኖች፣ ነጋዴዎች እና መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሠሩ መኾናቸውንም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የጸጥታ ችግር ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረስ ፈታኝ እንደኾነባቸውም አንስተዋል፡፡ ድጋፉ በወቅቱ እየደረሰ ባለመኾኑ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች እየተጎዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የመጠባበቂያ ድጋፋቸውንም በፈለጉት ወቅት ማድረስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የጉዳቱን መጠን ቀርቦ ለማጥናትም አስቸጋሪ እንደኾነባቸው ነው የገለጹት፡፡
የፀጥታውን ችግር በታሰበው መንገድ ለመፍታት እና በተቻለ መጠን ለመደገፍ አለማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡ በመኸር ምርት በሚኖረው የምርት ግምገማ የጉዳት መጠኑም እንደሚታወቅ ነው የገለጹት፡፡ ከሰዎች ባለፈ እንስሳትም ጉዳት እንደሚደርስባቸው የገለጹት ኮሚሽነሩ የሚደረገው ድጋፍ እንስሳትንም ታሳቢ ያደረገ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ ለአማራ ሕዝብ የሚያስብ ሁሉ የአማራ ሕዝብ እንዳይጎዳ መሥራት አለበትም ብለዋል፡፡ ግጭቶችን በማቆም ለተጎዱ ወገኖች መድረስ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረስ ረጂ ድርጅቶች እንዲረባረቡ እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡
የታቀደውን እቅድ ፈጥኖ መተግበር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ሀገር በቀል ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ሠው እንዳይራብና እንዳይጎዳ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ከቀጠለ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡ ኮሚሽኑም የገጠሙትን እና ሊገጥሙት የሚችሉትን ችግሮች ታሳቢ በማድረግ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!