
ባሕርዳር፡ መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ሠብአዊና ቁሳዊ ውድመት ያስከተለ መኾኑን አስታውቋል።
በዚህ ወቅት በብዙዎቹ አካባቢዎች የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም የበለጠ በማስፋትና በመጠቀም የሕዝቡን የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደ ወትሮው ሁሉ ሠላምን የወል ሀብት በማድረግ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ቢሮው ጥሪውን አቅርቧል።
ቀደም ሲልም ኾነ በዚህ ወቅት በክልሉ ያጋጠሙ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታትና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶች ጋር በመተባበር ለምትገነባው ኢትዮጵያ ትልቁ ቅድመ ኹኔታ ሰላም መኾኑን አመላክቷል።
ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች ከሰላም በተቃራኒ ግራና ቀኝ በተወጠሩ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች በወለዱት የግጭትና ቀውስ የሚፀና ማንነትና የሚገነባ ሀገር አለመኖሩን በአንክሮ ሊገነዘቡት የሚገባ ጉዳይ መኾኑን ቢሮው አመላክቷል። ይህንን እውነታ በመረዳት ሕዝቡ አኹን እንደታየው መላ ቀልቡን ወደ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት መመለስ እንዳለበት ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
ሕዝቡ የሀሳብ ልዩነትን በጠብመንጃ አፈሙዝ ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኀይሎችን ወደ ጎን በመተው በእጁ የገባውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን መሥራት ይጠቅበታል። ለዚህም ሕዝቡ የሰላም ጠባቂ ከኾኑ የፌደራልና የክልሉ የጸጥታ ኀይሎች ጋርም ተባብሮ መሥራት ይኖርበታል ብሏል ቢሮው በመልእክቱ። ከዚህ ጎን ለጎን የሰላም መታጣት ችግሩ እያስተጓጎለ ያለውን የልማት ሥራ እንደገና በእልህና በወኔ በፍጥነትና በጥራት በየደረጃው ካለ የመንግሥት ሠሪዎችና ባለሙያ ጋር በመተባበር ወደ መደበኛ ሥራው ሊገባ እንደሚገባም አሳስቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!