“ስጋት እየኾነ የመጣውን የወባ ስርጭት ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

36

ባሕር ዳር: መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ላይ ያለው የወባ ሥርጭት ከባለፉት ዓመታት 50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የወባ ስርጭት በከፍተኛ ኹኔታ በመጨመር ላይ ይገኛል። በአማራ ክልልም በተለይም ደግሞ በጎንደር እና በጎጃም አካባቢዎች ሥርጭቱ እየጨመረ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።

በክልሉ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራት መጠነኛ የወባ ስርጭት ፣ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ባሉት ወራት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የሚከሰትበት ወቅት ነው። ይሁን እንጅ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት እና የወባ ሥርጭት ወቅቶች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝ በኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አብርሃም አምሳሉ ነግረውናል።

በ2014 በጀት ዓመት 638 ሺህ ሕሙማን ሕክምና ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ በ2015 በጀት ዓመት የሕሙማኑ ቁጥር ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም በማሳያነት አንስተዋል። ይህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረው የወባ ሥርጭት 50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸውልናል።

ከሐምሌ/2015 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ወራት ደግሞ 213 ሺህ 253 ሕሙማን ሕክምና አግኝተዋል። ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት ያለው መረጃ ሲታይ ደግሞ የወባ ሥርጭቱ መጨመሩን ገልጸዋል። በመጀመሪያው ሳምንት 21 ሺህ 355 ሰዎች በወባ የተጠቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ 23 ሺህ 731 ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን አንስተዋል። ይህ መረጃ ካሉት አጠቃላይ የጤና ተቋማት 66 በመቶ ከሚኾኑት ብቻ የተገኘ መረጃ መኾኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና አዊ ብሄረሰብ አሥተዳደር ዞን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከነሐሴ/ 2015 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የመረጃ ልውውጥ መቋረጡን ገልጸዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የወባ ሕክምና ግብዓት ለማቅረብም አልተቻለም። በአካባቢዎቹ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እየተሠራ አለመኾኑን ገልጸዋል።

አሳሳቢ እየኾነ የመጣውን የወባ ሥርጭት ለመከላከል ማኅበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ለወባ መራቢያ ምቹ የኾኑ የአቆሩ ውኃማ ቦታዎችን ማፋሰስ ፣ ማዳፈንና ሳር የበዛባቸው አካባቢዎችን የማጨድ ሥራ መሥራት ይገባልም ብለዋል። ለ80 ወረዳዎች አጎበር መሠራጨቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ የቀረበውን አጎበር በአግባቡ መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።

ባለፈው ሰኔ/2015 ዓ.ም ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው ስድስት ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ገልጸዋል። አሁን ላይ ደግሞ ከፍተኛ ስርጭት ያለባቸው 190 ቀበሌዎች ላይ ርጭት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ቢሠራም እንደ ሀገር ባጋጠመው እጥረት እስከ አሁንም ርጭት አለመካሄዱን ነው የነገሩን።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር መወያየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
Next articleለአማራ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት አወንታዊ ፍላጎት ያለው ሁሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን እንዲወጣ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጥሪ አቀረበ።