
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።
ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን ከየካቲት 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት እየመራች ትገኛለች።
በዛሬው እለት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ የኢኒሼቲቩ ሊቀመንበር እና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ተገኝተዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ የትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኢኒሼቲቩ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና የልማት አጋሮች ተወካዮችም ታድመዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ እ.አ.አ 2019 ማብቂያ በአፍሪካ ቀንድ የፋይናንስ ሚኒስትሮች የተቋቋመ ነው።
በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም ባንክ እና አውሮፓ ኅብረት ድጋፍ የተቋቋመው ኢኒሼቲቭ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም በልማት ሥራዎች በተለይም በመሰረተ ልማት፣ ንግድ፣ አቅም ግንባታ መስኮች የተሻሉ ውጤቶችን ማምጣት ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ አድርጎ ይሠራል።
17ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ እ.አ.አ በግንቦት 2023 በግብጽ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!