
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በቆላማ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱን መዘገባችን ይታወሳል። የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ወገኖችም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ለአሚኮ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው በክልሉ እና ከሌሎች አካባቢ የተፈናቀሉ ከ1 ሚሊዮን በላይ ወገኖች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልፀዋል።
ኮሚሽነሩ በክልሉ በተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱንም አስታውቀዋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን አራት ወረዳዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱንም ተናግረዋል። በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርም በሰሃላ ሰየምት ወረዳ የከፋ ችግር መኖሩንም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሌሎች ወረዳዎችም ችግር መከሰቱንም ተናግረዋል።
ዲያቆን ተስፋው በማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዝናብ እጥረት መከሰቱን ነው የተናገሩት። ሰሜን ሸዋ ላይም በግሪሳ ወፍ ወረራ ምክንያት ችግር መኖሩን አስታውቀዋል።
በድርቁ ምክንያት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር 1 ሚሊዮን መድረሱንም ተናግረዋል። ዓለም አቀፍ ረጅ ድርቶች ድጋፍ ማቆማቸውንም ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።
የክልሉ መንግሥት ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የፌዴራል መንግሥትም በመጠለያ ለሚኖሩ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል። በጸጥታ ችግር ምክንያት ድጋፍ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።
የክልሉ አደጋ መከላከል ግብረ ኃይል ነባራዊ ኹኔታውን ገምግሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል። እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመኾኑ ተጨማሪ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ኮሚሽነሩ የተሻለ ምርት ያገኙ አርሶ አደሮች፣ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች እና ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የጸጥታ ችግሩ ድጋፍ ለማድረግ እና በበቂ ኹኔታ ለመሥራት አዳጋች እንዳደረገውም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!