
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት (ITU) ከመስከረም 22 እስከ 24/2016 ዓ.ም የሚያካሂደውን የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባዔ በአዲስ አበባ ጀምሯል።
ጉባዔው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ እና ሌሎች የኅብረቱ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ነው መካሄድ የጀመረው።
ጉባዔው “ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለዘላቂና ፍትሐዊ መጻኢ ጊዜ የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ማፋጠን” የሚል መሪ ሀሳብ ይዟል።
ጉባዔው በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣትና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ለመምከር ያለመ መኾኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለአህጉሪቷ መጻኢና ዘላቂ የዲጂታል እድገት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የልማት ግቦች መሳካት ያለው ሚና ላይ ምክክር እየተደረገበት ይገኛል ።
በጉባዔው ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት፣ በአፍሪካ እየተተገበሩ ያሉ የዲጂታል ትስስር ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ደረጃን እና ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ውይይት ይደረግባቸዋል።
የኅብረቱ የአፍሪካ አባል ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማትና የልማት አጋሮች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም በጉባዔው ላይ እየተሳተፉበት ነው።
ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት አንዱ ሲኾን የተቋቋመው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1865 ነው።
ዋና መሥሪያ ቤቱን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው ኅብረቱ በዋናነት በኢንፎርሜሽንና ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረቱን በማድረግ ዓለምን የማስተሳሰር ግብ ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ኅብረቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ 193 አባል ሀገራት አሉት።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!