የ2016 ዓ.ም ትምህርት ዘመን በተሳካ ኹኔታ መጀመሩን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

98

ባሕርዳር፡ መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ በተሳካ ኹኔታ መጀመሩን ትምህርት መምሪያው ገልጿል።

ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁሶችን አሟልተው በትምህርት ገበታቸው ተገኝተው የመማር ማስተማር ሂደቱን በጥሩ ኹኔታ መጀመራቸውን የከሚሴ ሰዳሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገልፀዋል።

የሰዳሳ ትምህርት ቤት የጅኦግራፊ መምህር እና ዩኒት መሪ አቶ ለሊሳ አመንቴ እንደተናገሩት ተማሪዎች በተሳካ ሁኔታ ተመዝግበው በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ይገኛሉ ። መምህራን በየትምህርት ክፍሉ በመወያየት የቅድ መዝግጅት ሥራዎችን በመሥራት የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ለ2016 የትምህርት ዘመን በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የሰዳሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት ዘይነባ መሐመድ መምህራን በሥራ ገበታቸው ተገኝተው የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጀምሯል ሲሉ ገልጸዋል።

ከ75 በመቶ በላይ ተማሪዎች ተገኝተው በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ናቸው ብለዋል። በቀጣይ ቀናቶች አጠቃላይ የተመዘገቡ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አቶ አብዱ አሕመድ እንደገለፁት በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች ባሉት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጀምሯል። የተማሪ መቀበል አቅም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እና ጥሩ አፈፃፀም የታየበት ነው ብለዋል።

አንደኛ ደረጃ ጥቅል ቅበላ 94 በመቶ እንደሆነ አሳውቀዋል። ዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ የሚገኘውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ምዝገባ ለማሻሻል በርብርብ እየሠሩ መኾኑንም አሳውቀዋል።

ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የመጽሐፍ እጥረት በዚህ ዓመትም እንዳይቀጥል ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር መፍትሔ ማስቀመጥ እንደታቻለም ገልጸዋል። በቂ መጽሐፍት መግባታቸውን መጥቀሳቸውን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአረጋዊያንን አስመልክቶ ለወጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ትኩረት እንዲሰጥ የአማራ ክልል ሴቶች እና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጠየቀ።
Next article“ትምህርት ቤቶች የ2016 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራቸውን ጀምረዋል” የጎንደር ከተማ ሥተዳደር