
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አረጋዊያን ላይ የሚደርሰውን ችግር እና የመብት ጥሰት ከማጋለጥ ባለፈ ተገቢውን ክብር እና እንክብካቤ መስጠት እንደሚገባ ቢሮው አሳስቧል።
ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን መስከረም 21/2016 ዓ.ም “የአረጋውያን መብት ማክበር ትውልድን ለማሻገር” በሚል መሪ መልእክት በመከበር ላይ ነው፡፡
የቢሮው የሕዝብ ግኝኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሃኑ እንዳሉት ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን ሲከበር ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ከመዘከር ባለፈ ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ፣ ተገቢውን እንክብካቤ መስጠት እና ልምድና ተሞክሯቸውን በመቅሰም ለመጭው ትውልድ ማስቀጠል ይገባል።
በዚህ ወቅት አረጋዊያን በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች መጋለጣቸውን አንስተዋል። በተለይም ደግሞ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የመጀመሪያዎቹ ተጎጅዎች መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ማኅበረሰቡ በአረጋውያን ላይ የሚደርሰውን ችግር እና የመብት ጥሰት ከማጋለጥ ባለፈ ተገቢውን ክብር እና እንክብካቤ መስጠት ይገባልም ብለዋል። በተለይም ደግሞ የፍትሕ ተቋማት አረጋዊያንን አስመልክቶ የወጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲከበሩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
የመንግሥት ተቋማትም ከአረጋዊያን ባለፈ የሴቶች ፣ ሕጻናት እና አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በመርሐ ግብራቸው አካትተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
አረጋዊያን እያጋጠማቸው ያለውን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት ከባሕር ዳር ባለፈ በክልሉ በሚገኙ ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች የገቢ ማስገኛ ማእከላትን ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ እስከ አሁንም በማዕከላዊ ጎንደር ሳንጃ ወረዳ፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አረርቲ ወደ ግንባታ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የግንባታ ቦታ ተረክበው በዝግጅት ላይ መኾናቸውን አንስተዋል። ባለሃብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!