
የአፍሪካ ሰገነት፣ የኢትዮጵያ ሕብረ ውበት ከተተነበየለት ጊዜ ፈጥኖ አገግሟል።
የምድር ከፍታ፣ የምንጮች ጉያ፣ የውበት ሕብር፣ የተፈጥሮ ድንቅ ሚስጥር ነው፡፡ ሲያዩት ደስ በሚል ሐሴት አጎናጽፎ አሻግሮ ይመልሳል፤ መልካም ተስፋ ይለግሳል፡፡ የሕይወት ምግብም ያጎርሳል፤ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ።
‹‹ ሀገራችን ጎንደር ስሜን አምባ ራስ፣
ዋልያ የሚያሳድግ እያበላ ገብስ፤›› ተብሎለታል፡፡ ጭላዳ፣ ዋልያና ቀይ ቀበሮ በድንቅ ተፈጥሮ ሲያማትሩ ማየት ልክ የለሽ ውበትን ለማድነቅ ያስችላል፡፡ ‹‹እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ›› እንደሚሉ ጎበዛዝት ተያይዘው በጎንደር ሰማይ ሥር የሚገኙት የስሜን ተራራዎች ለኢትዮጵያ ውበት፣ ሀብትና በረከት ናቸው፡፡ ባዘቶ የመሰለ ነጭ ጉም በተራሮቹ ላይ ሲጎተት ሲታይ ደግሞ ሌላ ትንግርት ነው፡፡ እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ከተራሮቹ የሚምዘገዘጉት ምንጮችም አጃኢብ! ያሰኛሉ፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዓለማችን ከሚገኙ ውብ ስፍራዎች መካከል ከግንባር ቀደሞቹ የሚጠቀስ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ኢትዮጵያን የረገጠ ሀገር ጎብኚ በጎንደር ሰማይ ስር የሚገኘውን ይሄን ውብ ተፈጥሮ ያያል፤ በልዩ ገጽታውም ይደነቃል፡፡ በአምስት ወረዳዎች የሚገኙ 42 ቀበሌዎችን አካልሎ የሚገኘው ይህ ውብ ስፍራ ባለፈው ዓመት በፊት በሰደድ እሳት ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡
412 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለው የሚነገርለት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ 1 ሺህ 45 ሄክታር ያህሉ በእሳት ተቃጥሎ ነበር፡፡ ከቃጠሎው ማግስት በአካባቢው በተደረገ ጥናት ‹‹ፓርኩ መልሶ ለማገገም 10 ዓመታትን ሊጠብቅ ይችላል የሚል ›› ግምት ነበር፡፡ ፓርኩ በአንድ ዓመት ቆይታው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ስንል ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ‹‹ከቃጠሎው ማግስት ለተፈጥሮ ምቹና ወቅቱን የጠበቀ ክረምት ስለገባ ፓርኩ በቶሎ እንዲያገግም እድል ሰጥቶታል›› ብለዋል፡፡ ቃጠሎ የደረሰበት 70 በመቶ የሚሆነው የፓርኩ ክፍል የጓሳ ሳር ስለነበር በፍጥነት ማገገሙንም ነው የተናገሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት ቃጠሎ የደረሰበትንና ያልደረሰበትን የፓርኩን ክፍል ለመለየት እስከማይቻል ድረስ ማገገሙን አቶ አበባው ተናግረዋል፤ ‘ፓርኩ መልሶ ለማገገም 10 ዓመታትን ሊወስድ ይችላል’ የተባለው ትንበያ ልክ እንዳልነበርም አንስተዋል፡፡ ጉዳት ከደረሰበት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ክፍል ማገገሙን ነው ኃላፊው በማሳያነት የጠቀሱት፡፡
በቃጠሎው የቀይ ቀበሮ ምግብ የሆኑ የአይጥ ዝርያዎች ጉዳት ስላልደረሰባቸው ቀይ ቀበሮዎቹ ቃጠሎ ደርሶበት ወደነበረበት ስፍራ ቶሎ እንደተመለሱም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በፓርኩ ላይ ደርሶ የነበረው ቃጠሎ የሕዝብ አንድነት የታየበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ አበባው ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ፓርኩን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅዶች ተነድፈው እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በፓርኩ ላይ የእሳት አደጋ ሊነሳባቸው የሚችሉ ከጥር እስከ ግንቦት ያሉ ወራትን ታሳቢ በማድረግ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በየአካባቢያቸው በማከፋፈል እንዲጠብቁ መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
አሠራሩ ልቅ ግጦሽን እና ሌሎች ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል እንደሚያስችልም ታምኖበታል፡፡
ፓርኩ የእሳት አደጋ ከመድረሱ በፊት እና በ2012 ዓ.ም ኅዳር ላይ በተደረገ የደረቅና የእርጥብ ጊዜ ቆጠራ ከ18 ሺህ 500 በላይ ጭላዳ ዝንጀሮዎች ይገኛሉ፡፡ ለሰው አስቸጋሪ የሆኑ ስፍራዎችን ሳይጨምር በተደረገ ቆጠራ በአማካይ ከ73 በላይ ቀይ ቀበሮዎችና ከ645 በላይ ዋልያዎች በፓርኩ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ሰው በማይደርስባቸው አካባቢዎች የሚገኙ እንስሳት ሲጨመሩ የእንስሳቱ ቁጥር ከዚህ በላይ እንደሚጨምርም አቶ አበባው ተናግረዋል፡፡
እንደ ጽህፈት ቤቱ መረጃ ፓርኩ ውስጥ የተተከሉት ችግኞች በመጀመሪያ ደረጃ የመጽደቅ ምጣኔ 65 በመቶ ነው፡፡ በያዝነው ዓመት ያለፉት ስድስት ወራት 16 ሺህ 71 የውጭ ሀገር እና 1 ሺህ 10 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ፓርኩን ጎብኝተውታል፡፡ በግማሽ በጀት ዓመቱም 16 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ገደማ ገቢ መገኘቱን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ