” ግሸን በዓለም ብቸኛዋ መስቀለኛ ቦታ የግማደ መስቀሉ መገኛ በመኾኗ በዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ መሠራት አለበት” አቶ መስፍን መኮንን

61

ባሕርዳር፡ መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በተከተለ መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅት እየተከበረ ነው፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አቶ መስፍን መኮንን ለሕዝበ ምዕመኑ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ወሎ የጥንት የታሪክ ማኅዳር፣ የብርሃነ መስቀሉ ማረፊያ ቅዱስ ምድር፣ የመጀመሪያው ቅኔ የተዘረፈባት ቦታ፣ የበርካታ አድባራት መገኛ፣ የጥበብ ሊቆች መፍለቂያ እንደነበረች ተናግረዋል፡፡

በርካታ ቅዱሳን የፈለቁባት፣ አስበልጣ ክብር የሠጠቻቸው እነ ቅዱስ ነዓኩቶ ለአብ እና እነ ቅዱስ ላሊበላ የፈለቁባት ምድር መኾኗንም ተናግረዋል፡፡ ዮሃንስ ገብላዊ ቅኔ የደረሰባት፣ የመጀመሪያው መካነ አዕምሮ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም የተድባበ ማርያም መገኛ፣ አድዋ ላይ ዘምቶ ድል ያደረገው የደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት እና የሌሎችም ቅዱሳን መገኛ ድንቅ ምድር ናት ሲሉም አንስተዋል፡፡ ደሴ በሰላም፣ በደግነት እና በጀግንነት የሚታወቅ ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢም እንደኾነ አንስተዋል፡፡

ግሸን ደብረ ከርቤ ከቅድስና ምንጭነት አስከ ሥነ መንግሥትነት ያገለገለች ቦታ፣ የታሪክ እና የቅርሳችን አምባ መኾኗንም ገልጸዋል፡፡ የአባቶቻቻንን የመሪነት መንገድ የሕዝባችንን ትጋት ታሪክ እና ሃይማኖት ጠብቃ ለትውልድ ያስተላለፈች ታሪካዊ ቦታ መኾኗንም ጠቁመዋል አቶ መስፍን፡፡

ግሸን ደብረ ከርቤ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም በዓለም ብቸኛዋ መስቀለኛ ቦታ የግማደ መስቀሉ መገኛ መንገደ-ሰማይ በመኾኗ ከመስቀል እስከ ግሸን ደብረ ከርቤ ንግሥ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረባት በመኾኑ በዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብና የተሟላ መሠረተ ልማት እንዲሠራላት ጠይቀዋል፡፡

ወሎ የኢትዮጵያውያን ቃል ኪዳን፣ የአንድነት ቡራኬ፣ ድንቅ ማሕፀን ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ መውረድ ማይፈልግ፣ ገንዘቡን እና ነፍሱን ሳይሰሥት የሚሠጥ፣ በአንድነቱ የማይደራደር በደም እና በሥጋ የተጋመደ ማኅበረሰብ መኖሪያ ምድር መኾኗንም ተናግረዋል፡፡ ወሎ የመንፈሳዊነት ከፍታ የመቻቻል አብነት የውሕደት ናሙና የጥበብ ማዕድ እንደኾነችም ተናግረዋል፡፡

ከታሪኩ የሚሸሽ እና ከታሪኩ የሚጣላ የትም አይደርስም፤ ሚዛናዊ ትውልድ መፍጠር የሚቻለው አወንታዊ እና አሉታዊ ችግሮችን አውቀን ስንፈታ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ከታሪክ የሚጣላ ትውልድ አዲስ ታሪክ መሥራት አቅም እንደማይኖረውም አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ መሠረት የሌለው ቤት እንደሚፈርስ ኹሉ ታሪክ የሌለው ሀገርም መነሻም መድረሻ እንደሌው ጠቁመዋል፡፡ ከታሪክ ከመጣላት ታሪክን አውቆ የተሳሳተውን ማስተካከል እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡ ነባሩን ታሪካችንን ጥለን ዓዲስ ታሪክ ሠርተን ማለፍ እንደማንችልም አቶ መስፍን ተናግዋል፡፡

ሰብዓዊ ቀውስ ደረሰብን ብለን ማልቀስ ሳይኾን ችግሩን ማወቅ እና መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከቀደምት አባቶቻችን ያገኘነውን እውቀት ተጠቅመን የደረሰብንን የሰላም እጦት ልንፈታ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ወጣቶች የአባቶቻቸውን ፍኖት ተላብሰው ለሀገራቸው ሰላም የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- በትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዲጅታል የክፍያ አማራጮች መስፋፋት የተነሳ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ቀንሷል።” የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር)
Next articleአረጋዊያንን አስመልክቶ ለወጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ትኩረት እንዲሰጥ የአማራ ክልል ሴቶች እና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጠየቀ።