
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የዲጅታል የክፍያ አማራጭ በመስፋፋቱ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር እንዲቀንስ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ በዲጂታል የክፍያ አማራጮች አማካኝነት በዓመት እስከ አራት ትሪሊዮን ብር እየተዘዋወረ መኾኑን አስታውቀዋል። እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) ሁለተኛውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ባለፉት ሁለት ወራት በከፍተኛ ኹኔታ መቀነሱን አንስተዋል።
ዲጂታል የክፍያ አማራጮች በከፍተኛ ኹኔታ እየተተገበሩ በመኾኑ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ሊቀንስ እንደቻለ አመላክተዋል። በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች በከፍተኛ ኹኔታ እየተስፋፉ ነው ያሉት ዶክተር እዮብ፤ በዓመት እስከ አራት ትሪሊዮን የሚደርስ ብር በዲጂታል የክፍያ አማራጮች እንደሚዘዋወር አመላክተዋል።
መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረግባቸው ግብይቶች በዲጂታል እንዲከናወኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከ 170 በላይ የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ውስጥ መግባታቸውን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ግብ ለማሳካት በመንግሥት አገልግሎቶች፣ በንግድ ሥራዎች የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን በዲጅታል የክፍያ አማራጮች መጠቀምና የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ማስቀረት ይገባል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች የዕለት ተዕለት ግብይታቸውን ጥሬ ገንዘብ ይዘው መሄድ ሳያስፈልጋቸው በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የሚፈልጉትን ሥራ እያከናወኑ መኾኑን አመላክተዋል።
በሀገሪቱ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ዘመን ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች በማስተዋወቅና የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ የራቀ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል። በቀጣይም የክፍያ ሥርዓትን ማዘመንና ተደራሽነቱን የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ዲጂታል የክፍያ አማራጮች ወጪን በመቆጠብ፣ የፋይናንስ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለማስቀረት፣ የዲጂታል ግብይት ተደራሽነትን ለማስፋፋትና ግልጽነት ያለው ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ከተቻለ የንግዱን ዘርፍ አገልግሎት ማሻሻል እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ እንዲኾኑ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። ኢፕድ እንደዘገበው ሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዲጂታል የፋይናስ ሥርዓትን የማጠናከር ዓላማ እንዳለው ዶክተር እዮብ አስታውቀዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አራት ቁልፍ ምሰሶዎች እንዳሉት የጠቆሙት ዶክተር እዮብ፤ የማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት፣ የግሉ ዘርፍ ንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል፣ የአየር ንብረትን በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ብቃት ያለው የሲቪል ሰርቪስ መፍጠር ላይ ትኩረት መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!