“ጤና ሚኒስቴር ከአጋሮቹ ጋር የወጣቶች ጤና እንዲሻሻል አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው” የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሠ

34

ባሕር ዳር: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 4ኛው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ከመስከረም 20 እስከ 22 /2016 ዓ.ም እየተካሄደ የሚገኘው የጤና ፎረሙ “ጠንካራ አጋርነት ፣ ትርጉም ያለው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ለተሻለ ጤና የሚል መሪ መልእክት ተቀርፆለታል።

በፎረሙ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ፣የክልል ጤና ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች ፣ የአፍሪካ ኅብረት ፣ በጤና ላይ የሚሠሩ ተቋማት ተወካዮች፣ ከዩኒሴፍ ፣ ከዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤ ፣ ከዓለም ጤና ድርጅት ፣ከኢትዮጵያ ወጣቶች ፣ በጤና ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ካውንስል ፕሬዚዳንት ወጣት ቶፊቅ እስማኤል ይህ ቀን የኛ የወጣቶች ነው ፤ ትርጉም ያለው ተሳትፎና አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና የምናደርግበት ነው ብሏል። አያይዞም ኢትዮጵያ በ2030 ያቀደችውን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንድታሳካ ወጣቶች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ነው ያለው።

ኢትዮጵያ በአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ላይ የጀመረችውን ሥራ እና አሁን 4ኛ ላይ በደረሰው የጤና ፎረም ከዓለም ጤና ድርጅት ቀድማ እየሠራች ነው ብለዋል። በቀጣዩ ዓለም አቀፍ ፎረም ዋነኛ ተዋናይ ትኾናለች ነው ብለዋል በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ፣ሕፃናት ፣ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና መሪ ሥራ አስፈጻሚ መሠረት ዘላለም (ዶ.ር)።

ጤና ሚኒስቴር ከክልሎችና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመኾን የወጣቶች ጤና እንዲሻሻል አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ያሉት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሠ (ዶ.ር) ናቸው።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በየቀኑ በዓለም 3ሺህ አፍላ ወጣቶች ልንከላከላቸው በምንችላቸው የጤና እክሎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ስለመኾናቸም ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ቀድማ በመገንዘብ ትኩረት ሰጥታ እየሠራችበት እንደኾነም አስገንዝበዋል።

አዲስ የጤና ዕቅድ በማዘጋጀት አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው ኾኗል ያሉት ሚኒስትሯ በዚህም የወጣቶችን ተሳትፎ የሚያጎለብት የተሳትፎ ሰነድ ማዘጋጀት ተችሏል ነው ያሉት።

ወጣቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃ የሚያገኙባቸው የቴክኖሎጂ አማራጮች እንደ “የኔታ አፕ” ጎልብተው አገልግሎት እየሰጡ ስለመኾናቸው ዶክተር ሊያ አብራርተዋል፡፡ ለወጣቶች የጤና አገልግሎት መስጠት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በቅንጅትና ትርጉም ያለው ተሳትፎን የሚያረጋግጥ አጋርነት ከሀገር አቀፍና ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር በመፍጠር የወጣቶች ጤና እንዲሻሻል በተለይም በኢንቨስትመንቶችና ኢንዱስትሪዎች ያሉ ወጣቶች ተደራሽ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ትኩረት፣ ድጋፍና ክትትል የሚፈልጉ ስለመኾናቸው ገልጸዋል።

ወጣቶች የሚገጥሟቸውን ውስብስብ ፈተናዎች በግል ወይም በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ ባለመኾኑ አካላዊና ስሜታዊ ደኅንነታቸውን መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች ተቀራርቦ ለመነጋገርና ለመመካከር ምቹ ኹኔታ ሊፈጠርላቸው ፤ ተሳትፏቸውም ትርጉም ያለው እንዲኾን ማድረግ ይገባል ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ አጋር አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

ወጣቶች ራሳቸውን ለጉዳት ከሚያጋልጧቸው ነገሮች በተለይም ከአቻ ግፊት ፣ ከአደንዛዥ ዕፆችና ሌሎችም ጌጂ ልምዶች መጠበቅ እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ ወጣቶች የዛሬም የነገም መሪዎችና ሀገር ተረካቢዎች በመኾናቸው ሁለንተናዊ ደኅንነታቸውንና ጤንነታቸውን መጠበቅ የሁልጊዜ ሥራ መኾን እንደሚገባውም አስረድተዋል።

በመድረኩ የተገኙት ዓለምአቀፍ ተቋማት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም እንዲመጣና የሰው ደም መፍሰስ እንዲቆም በሃይማኖት መበርታትና በጸሎት መትጋት ይገባል” ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ
Next article“በዲጅታል የክፍያ አማራጮች መስፋፋት የተነሳ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ቀንሷል።” የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር)