
ባሕርዳር፡ መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል በእየተከበረ ነው፡፡ ምዕምናንም ወደ መስቀለኛው ተራራ ከመስቀሉ በረከት ለመቀበል ተሰባስበዋል፡፡ በአንድነትም ስለ ሀገራቸው ሰላም በጸሎት ሲበረቱ አድረዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ አባታዊ ትምህርት ያስተላለፉት የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ኢትዮጵያ ለመስቀሉ፣ ለሀገር፣ ለሃይማኖት ክብር ያላቸው አባቶች እንደነበሯት እና እንዳሏት ተናግረዋል፡፡
አራቱም ንፍቅ የኢትዮጵያ መሬት ነው፤ በየትኛውም አቅጣጫ የሚፈጠር ችግር የኢትዮጵያዊያን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሆነን መገኘት አለብንም ብለዋል በመልእክታቸው፡፡ ስለ ሀገራችሁ ኢትዮጵያም ጸልዩ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው፡፡
ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር ሀገር ናት፣ ኢትዮጵያ ያለችው በእግዚአብሔር ኃይልና በልጆቿ ጸሎት ነውም ብለዋል፡፡ “እባክችሁ ስለ ሰላም በር ክፈቱም” ነው ያሉት በመልእክታቸው፡፡
ሀገራችንን ከፍ አድርገን እና ሰው ሰርተንባት እንለፍ ሲሉም አሳስበዋል፡፡ በሃይማኖት ጠንካራ መሆን እና በጽናት መቆም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በወሎ አካባቢ የረቀቀ ምስጢር ያለባቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና ቅዱሳን አበው እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ በምድሯ ሰላም እንዲሰፍን፣ ጦርነት እንዲጠፋም ተመኝተዋል፡፡
ምዕመናን የአባቶቻችሁን ሥም የሚያዋርዱና ዝቅ የሚያደርጉ ሰዎችን እንዲያውቁባቸውና ብልህ እንዲሆኑም አስግንዝበዋል፡፡ የቤተክርስቲያኗን አባቶች መስደብና ማዋረድ ጀግንነት አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ወደ ግሸን የመጣ ሁሉ በረከትና ረድኤት እየተቀበለ እንደሚመለስም ገልጸዋል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም የቅዱስ መስቀሉና የቅዱሳን መቀመጫ መኾኗንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በረከት የተሰጣት አምላክ የመረጣትና የጠበቃት ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
እባካችሁ መገዳደል ይቁም፤ ዓለም በደም እየተለወሰች ነውም ብለዋል ብፁእነታቸው በመልእክታቸው፡፡ ሰላም እንዲመጣና የሰው ደም መፍሰስ እንዲቆም በሃይማኖት መበርታትና በጸሎት መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!