
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓመታዊው የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓል በተራራዋ እመቤት አምባ ላይ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአራቱም አቅጣጫ የተሰባሰቡት ክርስቲያኖች ክርስትናቸውን በክርስቶስ ግማደ መስቀል ሥር ቆመው አድምቀውታል፡፡
በግሸን አምባ ለተሰባሰቡት ክርስቲያኖች ወንጌልን የሰበኩት የበጎቹ እረኛ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ብፁእ አቡነ ኤርሚያስ ናቸው፡፡ ግሪካዊያን በፍልስፍና እና እውቀት፤ አይሁዳዊያን ደግሞ ወደ ብሉይ ኪዳን አዘንብለው ምልክትን ብቻ በመሻት ሰንፈው ነበር ያሉት ብፁእ አቡነ ኤርሚያስ ቅዱስ ጳውሎስ ቆሮንጦሳዊያንን “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” ሲል አስተማራቸው ይላሉ፡፡
ቆሮንጦስ በጥንታዊቷ ፋርስ በአሁናዊቷ ቱርክ ኤፌሶን አውራጃ በግሪክ፣ በአቴና እና መቄዶኒያ መካከል የምትገኝ እና ከቀደምቷ የእውቀት ከተማ አቴና 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ይላሉ፡፡ ቆሮንጦስ በወቅቱ 600 ሺህ ገደማ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ነበረች የሚሉት አቡነ ኤርሚያስ ቅዱስ ጳውሎስ በሁለተኛው ሐዋሪያዊ ጉዞ ሕዝቦቿን ከፈጣሪያቸው ጋር እንዳገናኘላቸው ይታመናል ብለዋል፡፡
ብፁእ አቡነ ኤርሚያስ ቆሮንጦሳዊያን ከእግዚያብሔር ጋር የተገናኙት በሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ግን ነገሥታቶቻችን ሳይቀር ሕዝቡን ከፈጣሪው ለማገናኘት የበረቱ ነበሩ ብለዋል፡፡ አባት እና ልጅ ስለእግዚያብሔር መስቀል ፍፁም አንድ አይነት ሃሳብ ይዘው ከሀገር ሀገር በመንከራተት ከፈጣሪ እንድንገናኝ ምክንያት ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
አባቶቻችን ለትውልድ የሚቆረቆሩ፣ ለሀገር የሚያስቡ እና ለሃይማኖታቸው የጸኑ ነበሩ ያሉት አቡነ ኤርሚያስ ንጉሡ ዓጼ ዳዊት ከክርስቶስ ግማደ መስቀል ይልቅ በርካታ መጠን ያለው ወርቅ እና ብር በእጅ መንሻ ቀርቦላቸው ነበር ይላሉ፡፡ “እኛን ክርስቶስ ያዳነን በብርም በወርቅም አይደለም፤ መስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ እንጂ” በሚል የክርስቶስ ግማደ መስቀል እንዲሰጣቸው በዲፕሎማሲም በኃልም መበርታታቸውን ያነሳሉ፡፡
አቡነ ኤርሚያስ በትምህርታቸው “መስቀሌ የሚቀመጠው በመስቀል ላይ ነው” የሚል ራዕይ የተገለጸላቸው ንጉሥ ዳዊት መስቀሉን በተባሉት ቦታ ሳያደርሱ በስጋ ቢያርፉም “መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር” የተባሉት ልጃቸው ንጉሡ ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግሸን አድርሰውታል ብለዋል፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በግሸን አምባ ላይ የመሰባሰባቸው ምስጢር የአባት እና ልጅ ጽናት መሆኑን በማንሳት፡፡
የክርስቶስን መስቀል በመስቀለኛ ቦታ ላይ ለማስቀመጥ ሦስት ዓመታት መንከራተት ለብዙዎች ሞኝነት ይመስል ነበር ያሉት አቡነ ኤርሚያስ አባቶቻችን ሞኝ ሳይሆኑ ብልሆች እንደነበሩ ግን ዓለም ዘግይቶም ቢሆን አውቆታል ነው ያሉት፡፡
ዛሬ በዚህ ቅዱስ ስፍራ የተሰበሰባችሁ እናንተም ከሀገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር አትሂዱ ተብላችሁ ነበር ያሉት ብፁእነታቸው የመጣችሁት ሞኝ ሆናችሁ ሳይሆን ብልሆች ስለሆናችሁ ነው ብለዋል፡፡ ስለመስቀሉ መከራ እንኳን ቢመጣ ለመቀበል መዘጋጀት ብልህነት መሆኑን በማንሳት፡፡
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የምስጢሩ እና ክብሩ ሳጥን አድርጓታል” ያሉት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያ ሊቀ ነብያት ሙሴ በሲና የተቀበለው ጽላት እና ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ዘመን ያለን ኢትዮጵያዊያን በተሰጠን አደራ ልክ ታላቅ ኾነን መገኘት አለብን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተሰጣት አደራ ታላቅ ሀገር መሆኗን የሚያመላክት እና ጣኦት በኢትዮጵያ እንደማይመለክ የሚያሳይ ነው ያሉት ብፁእ አቡነ ኤርሚያስ አደራ ማክበር፣ የተሰጠንን ክብር መጠበቅ ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡ ጣኦት ማምልክ ሲባል ግዑዝ ነገር ማምለክ ብቻ አይደለም ያሉት ብፁእነታቸው ዘረኝነት፣ ፖለቲካ፣ ጥቅምን ማሳደድ፣ ሥልጣንና ሌሎቹ ዓለማዊ ስግብግብነቶች ሁሉ ጣኦታት ናቸው ነው ያሉት፡፡
በዓለም ላይ የተከሰቱ ጦርነቶች ሁሉ መቋጫቸው ሰላም ነው ያሉት ብፁእነታቸው ኢትዮጵያዊያን ምን ያክል ሕዝብ ሲሞት ነው ወደ ሰላም እና መነጋገር የምንመጣው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም ለእውነተኛ ሰላም እርቅ እንዲተጋ ጠይቀዋል፡፡
ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ ልዩነቶችን ሰላማዊ ወደ ኾነ የሃሳብ ገበያ አምጥቶ መነጋገር ከጥንት አባቶቻችን የወረስነውና እውነተኛው የሰላም መንገድ ነው ብለዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!