በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የጸጥታ ችግሮች ትልቅ ፈተና እንደኾኑበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

82

ባሕር ዳር: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአራት ክልሎች እና በሁለት ከተማ አሥተዳደሮች የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦችን እና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎችን ማጠናቀቁን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በቀሪ አካባቢዎች ከ2016 ዓ.ም አጋማሽ ቀድሞ የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦችን እና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እየሠራ ነው ተብሏል።

በሕዝብ እና መንግሥት፤ በሕዝብ እና ሕዝብ መካከል መተማመን እንዲኖር የሚያስችል ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በማለም የካቲት 14/2014 ዓ.ም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የውስጥ አደረጃጀቱን የማጠናከር፣ የተለያዩ ዘርፎችን እና አማካሪ ኮሚቴዎችን የማቋቋም ሥራዎችን ሠርቷል ተብሏል፡፡ የሦስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ጸድቋል ያሉት ኮሚሽነሩ የኮሚሽኑ የሥራ አቅጣጫ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ክልሎች መውረዱንም ነው የገለጹት።

ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችሉ የአጀንዳ መነሻ ሃሳቦችን ከምሁራን እና ከምርምር ተቋማት በተጨማሪ በየወረዳው እስከ 10 የሚደርሱ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ተሳታፊዎቹ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሕዝብ የተመረጡ ናቸው ተብሏል፡፡

የተመረጡት የኅብረተሰብ ክፍሎችም የአጀንዳ መነሻ ሃሳቦችን ከመረጣቸው ማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት እየለዩ መኾናቸውን ኮሚሽነሩ ዶክተር ዮናስ በተለይ ለአሚኮ ገልጸዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሀረሪ ክልል እና በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደሮች የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦችን እና በክልል ደረጃ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታ ተጠናቅቋል ብለዋል። በእነዚህ ክልሎች እስከ 70 ሺህ ሕዝብ ማወያየት ተችሏል ተብሏል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በቀሪ ክልሎች ከመጪው ጥር ቀድሞ የተሳታፊ እና የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦችን ልየታ በማጠናቀቅ በ2016 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በክልል ደረጃ ምክክር ለማካሄድ እየተሠራ ይገኛል። ክልላዊ ምክክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጨረሻ ምክክሩ የሚካሄድ ይኾናል።

ኮሚሽነሩ ዶክተር ዮናስ እንደሚሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነሱ ዋና ዋና የአጀንዳ መነሻ ሃሳቦችን ኮሚሽኑ ከአማካሪ ቦርዱ ጋር በመኾን በየፈርጁ የመለየት ሥራ ይሠራል። ኮሚሽኑ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሥራዎቹን ለማጠናቀቅ የሀገሪቱን ነባራዊ ኹኔታ ባገናዘበ መንገድ እቅዶችን የማስተካከል ሥራ መሥራቱን ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የጸጥታ ችግሮች ለምክክር ኮሚሽኑ ትልቅ ፈተና መኾናቸውን ያነሱት ዶክተር ዮናስ ማኅበረሰቡ ውክልና እንዲያገኝና የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦች እንዳይቀሩ በሀገር ሽማግሌዎች እና በምሁራን ጭምር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎች የሚያግዙ የአካባቢውን ባሕል፣ የማኅበረሰቡን ሥነ ልቦና፣ ወግ እና ታሪክን መሠረት ያደረገ አማካሪ ኮሚቴ በየክልሉ ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ነው ኮሚሽነር ዮናስ የገለጹልን።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያለመ አህጉር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
Next article“እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የምስጢሩ እና ክብሩ ሳጥን አድርጓታል” ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ