የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያለመ አህጉር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

54

አዲስ አበባ: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምክክር መድረኩን የከፈቱት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሳንዶካን ደበበ የተፈጥሮ ሀብት መሸርሸር ችግር ዘርፈ ብዙ እና ዓለማቀፋዊ ስጋት መኾኑን ተናግረዋል። በተለይም ለአፍሪካ እና ለሌሎች ላላደጉ ሀገራት ዋነኛ ተግዳሮት ነው ብለዋል። የአፍሪካ አህጉር ለአየር ንብረት መዛባት አስተዋፆኦ እምብዛም ቢኾንም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች እና የችግሩ ዋነኛ ተጎጂ ኾናለች ነዉ ያሉት። በዚህም ኀላፊነት ያልተሞላበት የተፈጥሮ ሀብት ብዝበዛና የሥነ ምህዳር መዛባት እንዲኖር ሁነኛ አስተዋፆኦ አድርጓል ብለዋል።

ይህን ችግር ደግሞ መቀልበስ የሚያስችል አቅም አፍሪካ የሌላት መኾኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው። አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ታዳጊ ሀገራት ፓሊሲ ቀርፀው እና ማስፈጸሚያ ስልት ነድፈው እየሠሩ ቢኾንም ያደጉት ሀገራት ለዚህ ተግባር የሚያደርጉት የፋይናንስ ድጋፍ ግን በቂ አደለም ብለዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ኹኔታ ውስጥ ኾኖም እንደ ግሎባል ኢንቫይሮመንት ፈሲሊቲ አይነት ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ የሚመሠገን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ይህን ችግር በዘላቂነት ለመሻገር ከተከተለችው የሀገሪቱ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ልዩ ቦታ በመስጠት አካታ እየሠራች መኾኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

የዓለም አቀፍ የአካባቢ ስምምነቶች ድርድር ማስተባበሪያ ዳይሬክተር መንሱር ደሴ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል በባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ያበረከተችው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመኾኑን ተናግረዋል። ሀገራችን መድረኩን እንድታዘጋጅ እና ሌሎች ሀገራት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ተመርጣለች ነው ያሉት።

በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ በታዳጊ የአፍሪካ ሀገራት ጉዳት እያስከተለ መኾኑን ተከትሎ በመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።

በጉባኤው ከ18 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወካይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ጉባኤው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የአከባቢ ፋሲሊቲ (GEF) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለዉጥ ማዕቀፍ ስምምነት (UNFCCC) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት አህጉራዊ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ያካሂዳል።
Next articleበአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የጸጥታ ችግሮች ትልቅ ፈተና እንደኾኑበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡