የደረቅ ወደቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡

747

ባሕር ዳር፡- ጥር 21/2012ዓ.ም (አብመድ) ለሰሜን ምስራቁ ክፍል አስመጭና ላኪዎች ትልቅ ፋይዳ እንዲኖረው ታስቦ የተገነባው የወረታ ደረቅ ወደብ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሆነ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ስምንተኛውን የደረቅ ወደብ ተርሚናል ግንባታ ባለፈው ዓመት መጋቢት መጀመሪያ ላይ በወረታ ከተማ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ በ100 ሚሊዮን ብር የመጀመሪያ ዙር ግንባታው የተጀመረው የወረታ ደረቅ ወደብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ድርጅት በተለይ ለአብመድ አስታውቋል፡፡

በድርጅቱ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ የወረታ ደረቅ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ሲጀምር በምድር ላይ ብቻ በቀን 937 ኮንቲነር የማስተናገድ አቅም አለው ብለዋል፡፡ በዓመት ኮንቲነሮችን ሳይደራርብ መሬት ላይ ብቻ 16 ሺኅ 868 ኮንቲነር የማስተናገድ አቅም አለው፡፡

ኮንቲነሮች ሲደራረቡ እና ዘመናዊ ማሽነሪዎችን ሲጠቀሙ ደግሞ ቁጥሩ በሦስት እጥፍ ይጨምራል ነው ያሉት፡፡ የደረቅ ወደብ ግንባታው ዘርፈ ብዙ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንዳለው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በሱዳን በኩል ያለውን የወጭ ገቢ ንግድ ለማጠናከር ያግዛልም ብለዋል፡፡ ግንባታው ሙሉ በሙሉ በ21 ሄክታሩ ላይ ሲያርፍ 5 ሺኅ 355 ኮንቲነር በቀን እና 96 ሺኅ 390 ኮንቲነር በዓመት የማስተናገድ አቅም አለው ብለዋል አቶ አሸብር፡፡

የወረታ ደረቅ ወደብ በዋናነት ለሰሜን ምስራቅ አስመጭና ላኪዎች ወሳኝ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በወደብና ተርሚናሉ መሃንዲስ አቶ አስማማው ካሰው እንደገለጹት ደግሞ ወደቡ መሠረተ ልማቶች ተሟልተውለታል፡፡ ሥራው መጠናቀቅ የነበረበት ነሐሴ 12/2011 ዓ.ም ቢሆንም በወሰን ማስከበር ችግርና በክረምቱ ዝናብ ምክንያት ዘግይቷል፡፡ ወደቡ አሁን ላይ ለ29 ቋሚና ለ1 ሺህ 463 ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ እድል እንደፈጠረ ታውቋል፡፡

የደረቅ ወደብ ተርሚናሉ በሚቀጥለው በሚቀጥለው የካቲት መጀመሪያ ላይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ታቅዷል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በሁለተኛውና በሦስተኛው ምዕራፍ ቀሪ 17 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው የሚከናወን ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው እና ፍቃዴ ዋለልኝ

Previous articleየሰላማዊ ሰልፎቹ አንድምታ በምሁራን ዕይታ!
Next articleለማገገም 10 ዓመታት ይወስድበታል ቢባልም በስድስት ወራት የቀድሞ ፀጋውን ተጎናጽፏል፤ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ!