ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት አህጉራዊ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ያካሂዳል።

47

ባሕር ዳር: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኅብረቱ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ያዘጋጁት ጉባኤ “ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለዘላቂና ፍትሐዊ መጻኢ ጊዜ የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚካሄደው።

ጉባኤው በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣትና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት በሚቻልበት ኹኔታ ላይ እንደሚመክር ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለአህጉሪቷ መጻኢና ዘላቂ የዲጂታል እድገት እንዲሁም ለዓለም አቀፍና አህጉራዊ የልማት ግቦች መሳካት ያለው ሚና ላይ ምክክር እንደሚደረግም ገልጿል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት፣ በአፍሪካ እየተተገበሩ ያሉ የዲጂታል ትስስር ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ደረጃን የተመለከቱና ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ውይይት እንደሚደረግባቸውም ጠቁሟል።

ኢዜአ እንደዘገበው በጉባኤው ላይ የኅብረቱ የአፍሪካ አባል ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማትና የልማት አጋሮች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ አመላክቷል።

ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት አንዱ ነው ፤ የተቋቋመው እ.አ.አ በ1865 ነው።

ዋና መሥሪያ ቤቱን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው ኅብረቱ በዋናነት በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረቱን በማድረግ ዓለምን የማስተሳሰር ግብ ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል።

ኅብረቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ 193 አባል ሀገራት አሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትየጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሽምግልና ሥርዓቶችን አካትቶ ቢሠራ ምክክሩን ውጤታማ ያደርገዋል” የታሪክ ምሁሩ አየለ በክሪ (ዶ.ር)
Next articleየአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያለመ አህጉር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።