
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በርካታ መልካም የኾኑ እሴቶች ያሏት ሀገር ናት ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ገልጸዋል። የምክክር ኮሚሽኑ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸውን የሽምግልና ሥርዓቶች አካትቶ ቢጠቀም እንደ ሀገር የተያዘውን ምክክር ስኬታማ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።
በሀገራችን ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ በመጣ የሽምግልና ሥርዓት ሂደት ኢትዮጵያውያን በብዙ ተጠቃሚ መኾን ችለዋል። አንዱ የሌላውን ደም ላለማፍሰስም ኾነ ቂምና በቀል ላለመያያዝ የሀገሪቱ የሽምግልና ሥርዓት ዋና ድልድይ መኾናቸውንም አንስተዋል። ዛሬም ጠቀሜታቸው ጉልህ በመኾኑ ኮሚሽኑ በእንቅስቃሴው ሁሉ ሀገር በቀል ሽምግልናን ቢያካትት ለምክክሩ አጋዥ ከመኾኑ በተጨማሪ ለስኬታማነቱ ድርሻው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፤ በዚህ ረጅም ታሪክ ውስጥም ሕዝቡ አንዱ ከሌላው ጋር ተደበላልቆ ኖሯል። በደስታውም ኾነ በመከራው አብሮ ያሳለፈ ነው። በዚህ እንቅስቃሴው ውስጥ ያፈራቸው ብዙ ትውፊቶች እና እሴቶችም አሉት። እነዚህ እሴቶቹ ሊመጡ የቻሉት ደግሞ ሕዝብ አብሮ በመኖሩ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ምንም እንኳ በቋንቋ፣ በሃይማኖት እና በብሔሩ ቢለያይም አብሮ መኖርን ግን ያውቅበታል ፤ ጠላትም ቢመጣ እንዲሁ ተባብሮ ያንን ጠላት የሚያሸንፍ ሕዝብ ነው። ኮሚሽኑ እነዚህን እሴቶች እና የሕዝብ የሽምግልና ሥርዓቶች ሊጠቀምባቸው ይገባል ሲሉ ነው ምሁሩ የተናገሩት።
ግልጽ በኾነ መንገድ ተዋህደን ችግራችንን እንፍታው በሚል ታላቅ ዘመቻ ከተጀመረ እሱን አሻፈረኝ ብሎ ወደኋላ የሚቀር አካል አይኖርም ብለዋል ዶክተር አየለ።
የሀገራችንን የሽምግልና ሥርዓት እና የምክክር ባሕል የሚቃወም ካለ ደግሞ የሕዝብ ጠላት ይኾናል ፤ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ሕዝቡን የሰለቸው ነገር ቢኖር እርስ በእርስ መገፋፋትና ጦርነት ነው ብለዋል።
በእርስ በእርስ ጦርነት የምንጎዳው እንደ ሀገር ነው፤ ከዚህ ደግሞ ማንም ተጠቃሚ አይኾንም ብለዋል። በሀገራችን የሚከሰቱ ግጭቶች የውጭ ጠላትን ለመጋበዝ በጣም ምቹ በመኾናቸው ወደ ምክክርና ስምምነት በመምጣት ከዚህ አይነቱ ጎጂ አካሄድ መላቀቅ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።
ዶክተር አየለ ለኢፕድ እንደገለጹት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንደ ሀገር ከመቋቋም አልፎ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ወደ ዋና ሥራ በመግባት ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ የተሰጠው ኀላፊነት በእርሳቸው እምነት አነስተኛ ነው። ለአብነትም ኮሚሽኑ ውሳኔ ሊያሳልፍ የማይችል መኾኑን አንስተዋል። ለምክክር ኮሚሽኑ የበለጠ ሥልጣን እና ኀላፊነት መስጠት እንደሚገባም ሀሳባቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!