
ባሕር ዳር፡- ጥር 21/2012ዓ.ም (አብመድ) መንግስት የሕዝብ ውክልናውን በአግባቡ ሊጠቀምበት እና ሊያገለግልበት እንደሚገባ አብመድ ያነጋገራቸው ምሁራን ተናገሩ፡፡
ሕዝብ የመንግሥትን ትኩረት ይሻል የሚለውን ጥያቄ በተለያዩ መንገዶች ያቀርባል፡፡ በተለይም መንግሥት ቸልተኝነት አሳይቷል ብሎ በሚያምንባቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄውን በሲቪክ ማኅበራት፣ በተወካዮቹ ወይም በመረጠው መንገድ ቀርባል፡፡ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎችን ይዞ አደባባይ ይወጣል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ካልተፈታ የመሪውና የተመሪው ግንኙት የመሪነትና የተመሪነት ሳይሆን የባላንጣነት ይሆናል፡፡ እነዚህ ክስተቶች ደግሞ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ተስተውለዋል፡፡
የሕዝብን ጥያቄና ስነ ልቦና የተረዱ መሪዎች ዘመናቸውን አስረዝመው፣ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ሠርተው አልፈዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው እስካሁን ድረስ አድራሻቸው ያልታወቁ ተማሪዎችን በተመለከተ ሕዝብ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ የእገታ ድርጊቱን እና መንግሥትን ዝምታ በመኮነንም ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እና በዋሽግተን ዲሲ ሠላማዊ ሰልፎች ተካሄደዋል፡፡ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያለበት አስቀድሞ ለሚቀርቡት ጉዳዮች እና የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች ወይስ ይህ ሁሉ ታልፎ በሰልፍ ሲቀርቡ? ስንል ከዘርፉ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና አሥተዳደር ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ታምራት ቸሩ የሕዝቡ የአደባባይ ጥያቄ ተገቢነት ላይ ይስማማሉ፤ ወቅታዊ፣ አቀራረቡም ሰላማዊና ጨዋነትን የተላበሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው›› ያሉት ዶክተር ታምራት መንግስት ከሕዝብ፣ ሕዝብም ከመንግስት የሚጠብቀው ጉዳይ መኖሩን አንስተዋል፡፡ ሕዝብ ከመንግስት ከሚጠብቃቸው ጉዳዮች ዋነኛው ደግሞ ሰላምና ደኅንነቱን እንዲያስጠብቅለት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
መንግስት ማንነት ተኮር ጥቃቶችን የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰው በማንነቱ ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊነቱ ብቻ እንዲህ አይነት እኩይ ተግባር ሊፈጸምበት አይገባም›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ታምራት በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ በነበሩ ተማሪዎች ላይ የደረሰው ጥቃት ጉዳይም የአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ሀገሪቱ ሕዝቦች ጥያቄ መሆን እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡
መንግስት መሰል ድርጊቶችን በመቆጣጠር፣ ለሕዝቡ ወቅታዊ ተገቢና ግልጽ መረጃዎችን በማድረስና አጥፊዎቹ ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ በኩል ክፍተት እንዳለበትም ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ታዲያ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ጥያቄዎችን መጠየቁ አግባብ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ የሕዝብና የመንግስት ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን ከተፈለገ የሕዝብን ጥያቄ ማዳመጥ፣ ፈጣንና አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም ምሁሩ አሳስበዋል፡፡ ሕዝቡም ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ እንዳቀረበ ሁሉ ምላሹንም በትዕግስት መጠበቅ እንዳለበት ነው የመከሩት፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ ደግሞ ‹‹መንግስት ከሕዝብ ኮንትራት የተቀበለ ነው፤ የውል ሰጪውን ሥራ ቆጥሮ መቀበልና በሚገባው መንገድ መሥራት አለበት›› ነው ያሉት፡፡ ‹‹ሕዝብ ተቋም ገንቢ ነው፡፡ ‹በሕግ አምላክ› ለሚለው ቃል ክብር ይሰጣል፤ የጠየቀበትና ጠይቆ የተመለሰበት መንገድ የሕዝቡን ትልቅነት የሚሳይ ነው›› ሲሉ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
ሕዝብን የሚወክል ድርጅት በሕዝብ ስነ ልቦና ልክ የተቀረጸ መሆን መቻል አለበትም ብለዋል፡፡ በተለይም መንግስት የሕዝብ ውክልናውን በአግባቡ ሊጠቀምበት እና ሊያገለግልበት እንደሚገባ ነው ምሁራኑ በአጽንዖት የመከሩት፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ
ፎቶ፡- በኃይሉ ማሞ