“እናታችን እያሉ፣ ወደ ተራራው ይወጣሉ”

51

ባሕርዳር፡ መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አስቀድማ የተዘጋጀች፣ በደል በተደመሰሰበት አምሳለ መስቀል የተፈጠረች፣ ታቦታትን ያሳረፈች፣ ለግማደ መስቀሉ ማረፊያነት የተመረጠች፡፡ ግማደ መስቀሉ ያረፈባት፣ ቅዱሳን አበው የተጠለሉባት፣ የነገሥታቱ ልጆች እውቀትን የገበዩባት፣ ሃይማኖትን የተማሩባት፣ ሥርዓትን የሠሩባት፡፡

የተመረጡ ተራራዎች ጽላት ይወርድባቸዋል፣ የተቀደሱ ተራራዎች ቤተ መቅደስ ይታነጽባቸዋል፣ የተባረኩ ተራራዎች ግማደ መስቀሉ ያርፍባቸዋል፣ የተቀደሱ ተራራዎች ገዳማት ይገደሙባቸዋል፣ የተወደዱ ተራራዎች ቃል ኪዳን ይሰጥባቸዋል፣ ትንቢት ይነገርባቸዋል፣ ትንቢትም ይፈጸምባቸዋል፡፡ የተቀደሱ ተራራዎች ቅዱሳን አበውና እመው ይጸለሉባቸዋል፣ ያለ ማቋረጥ ስበሐተ እግዚአብሔር ይደረስባቸዋል፣ የአምላክ ስጋና ደም ይፈተትባቸዋል፤ የተቀደሱ ተራራዎች ሕግና ሥርዓት ይጸናባቸዋል፡፡

የተመረጡ ተራራዎች አምላክ ይገለጥባቸዋል፣ በተመረጡ ተራራዎች ጳጳሳት ይቀመጡባቸዋል፣ ነገሥታት ይከትሙባቸዋል፣ የነገሥታት ልጆች ልዑላን ይመላለሱባቸዋል፣ ሕግ እግዚአብሔርን ይማሩባቸዋል፣ የቤተ ክህነቱን እና የቤተ መንግሥቱን ጥበብ ይቀስሙባቸዋል፡፡ የተመረጡ ተራራዎች የአምላክ ቃል ይሰበክባቸዋል፡፡

ከተወደዱት ተወደደች፣ ከተመረጡት ተመረጠች፣ ከተከበሩት ተከበረች፣ ከተናፈቁት ተናፈቀች፡፡ ከተጠበቁትም ተጠበቀች፡፡ ነገሥታቱ ይቀመጡባታል፣ ፍርዳቸው የተስተካከለ እና ያላጋደለ ይኾን ዘንድ ይማጸኑባታል፣ ጥበብ ይሰጣቸው ዘንድ አምላካቸው ይለምኑበታል፡፡ መስቀል ኾና ተፈጠረች፣ መስቀል ኾና ኖረች፣ መስቀሉንም አኖረች፣ መስቀሉንም ትጠብቃለች፣ በመስቀሉም ምድርን እና ሕዝቧን ትባርካለች፣ ትቀድሳለች፣ በበረከትና በረድኤት ትመላለች ታላቋ ሥፍራ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም፡፡

በተቀደሰች ተራራ ላይ የተቀደሰች እመቤት፣ የተቀደሰው መስቀል እና የበዙ ቅዱሳን አሉባትና ምዕመናን እናታችን እያሉ ወደ ተራራው ይወጣሉ፡፡ በመስቀለኛው ተራራ አናት ከቅዱስ መስቀሉ ግርጌ ተሰባስበው ለምድር ሰላምና ፍቅር ይሰጥ ዘንድ አምላካቸውን ይማጸናሉ፣ በደልና መከራን ያርቅ ዘንድ ይለምናሉ፡፡

አጼ ካሌብ በአበው ዙፋን ላይ ተቀምጠው በሀገረ ኢትዮጵያ ላይ ነግሠዋል፡፡ እኒህ የተወደዱ ንጉሥ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚጠራ ኀያል ናቸው፡፡ ሕገ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ፣ ለአምካቸው የሚሰግዱና አምላክን የሚፈሩ ናቸው፡፡ አጼ ካሌብ በኢትዮጵያ ነግሠው በነበረበት በዚያ ዘመን በየመን ሀገረ ናግራን ይኖሩ የነበሩ ግፍ የበዛባቸው ምዕመናን ነበሩ፡፡ እነዚህ ምዕመናን ሮማውያንን ሽሽት ከኢየሩሳሌም የተሰደዱ ነበሩ፡፡ በዘመኑ አምላክን የማያመልክ አላዊ ንጉሥ ነግሦ ምዕመናንን ያሰቃያቸው ነበር፡፡ የምዕመናን መከራና ስቃይ በበዛ ጊዜ ከመከራና ከስቃይ ይታደጓቸው ዘንድ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለአጼ ካሌብ የተማጽኖ መልእክት ላኩ፡፡

አጼ ካሌብም ይሄን በሰሙ ጊዜ ለአምላካቸው አደራ ሰጥተው ምታ ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት ብለው፣ እጅግ የበዛ ጦራቸውን አስከትለው፣ በግርማና በሞገስ በቅዱሳን አበው እየተመሩ ወደ ናግራን ገሰገሱ፡፡ በዚያች ምድር ደማቸው በግፍ የሚፈስስ፣ አጥንታቸው የሚከሰከስ አሳዛኛ ምዕመናን ነበሩ እነሱን ይታደጓቸው፣ ጠላቶቻቸውንም ይቀጡላቸው ዘንድ ሄዱ፡፡

ኀያሉ ንጉሥ አጼ ካሌብ በዚያ በደረሱ ጊዜ ግፈኛውን ንጉሥ እስከ ሠራዊቱ ድል መትተው፣ ከሞት የተረፉትን፣ ከጥላ ያረፉትን ነጻ አውጥተው፣ በዚያች ሥፍራ ቤተ መቅደስ አሳንጸው ወደ መንበራቸው ተመለሱ፡፡ በዚያም ሥፍራ የቀደመ ስማቸው አባ ፍሊክስ የኋለኛው ስማቸው ፈቃደ ክርስቶስ የተባሉ ጽድቅን የተቸሩ፣ ስጋቸውን ያደከሙ፣ ነብሳቸውን ያበረቱ መናኝ መነኩሴ ነበሩ፡፡ እርሳቸውም በቅድስና የሚጠብቋቸው ሁለት ጽላቶችን ይዘው ነበር፡፡

አባ ፈቃደ ክርስቶስ ራዕይ ታያቸው ፣የብርሃን አምድ እንደ ፀሐይ እያበራ፣ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ድምጽ እያስፈራ፣ በአንዲት ሥፍራ ተተክሎ ታያቸው፡፡ ይሄም የብርሃን አምድ እየደጋገመ ይታያቸዋል፡፡ ቅዱሱ አባትም ራዕዩን እየጠበቁ ባለ ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም በራዕይ ተገልጣ ሁለት ጽላቶችን ይዘህ የብርሃን አምድ ወደ ተተከለባት ሀገር ሂድ አለቻቸው ይላሉ አበው፡፡

አባ ፈቃደ ክርስቶስም አሥራ ሁለት መነኮሳትን አስከትለው በራዕይ ወደታየቻቸው ሥፍራ ገሰገሱ፡፡ የእግዚአብሔር መላእክም ከፊት እየቀደመ ይመራቸዋል፡፡ በደከሙ ጊዜም ያበረታቸዋል፡፡ ፈቃደ ክርስቶስ የብርሃን አምድ ተተክሎባት ያዩዋት፣ ቅድስት ድንግል ማርያምም ይሄዱ ዘንድ ያዘዘቻቸው ያቺ ሥፍራ በእግዚአብሔር አዛዥነት፣ በመላእክቱ ጠባቂነት ስትጠበቅ ኖራለች፡፡ ዘመኑ እስኪደርስ ድረስም እየታሰበች ነበረች፡፡ በተራራው የብርሃን አምድ ተተክሎ ይታያል፡፡ አውራጃዎችን አቆራርጠው የእግዚአብሔር መላእክ እየመራቸው ወደ አንድ መስቀለኛ ተራራ ግርጌ ደረሱ፡፡

ወደ መስለቀኛው ተረራ ለመውጣት ባሰቡ ጊዜ የንብ መንጋ ተራራውን ሰፍሮበታል፡፡ ማሩም እጹብ ኾኖ ይታያል፡፡ አዕዋፋት ይዘምሩበታል፤ እንስሳት ያለ ከልካይ ይመላለሱበታል፡፡ ይሄንም ያዩት ደገኛው መነኩሴ ፈቃደ ክርስቶስ ተገረሙ፡፡ ይሄስ አምባሰልን ይመስላል አሉ፡፡ “አሰል” ማለት ማር ማለት ነው ይላሉ፡፡ የማር አምባ ሲሉ፡፡ የማር ሀገር፣ የቅዱሳን እና የባሕታውያን አድባር፡፡ ፈቃደ ክርስቶስ ወደ አምባው ወጡ፡፡ በራዕይ እንደታያቸው፣ ድንግል ማርያምም እንዳዘዘቻቸው ሁሉ አደረጉ፡፡ ጽላቶቹን በክብር አስቀመጡ፡፡ የዘመኑ ንጉሥ አጼ ካሌብም ገዳም አስገደሙባት፣ ሥርዓት አሠሩላት፣ አገልጋይና አሥተዳደርም ሾሙላት፡፡

እግዚአብሔር አስቀድሞ የመረጣት፣ ክብሩን ይገልጥባት ዘንድ የወደዳት፣ ልጆቹ ሁሉ ይሰባሰቡባት ዘንድ አስቀድሞ ያዘጋጃት የተቀደሰች፣ በአምሳለ መስቀል ያረፈች ቅድስት ሥፍራ ግሸን፡፡ ክብሩን ገለጠባት፣ የከበረው መስቀሉ ይቀመጥባት ዘንድ መረጣት፣ ቀደሳት፣ መርጦና ጠብቆ አዘጋጃት፡፡ አጋንትን የሚያቃጥላቸው፣ ሰማይና ምድርን ያስታረቃቸው፣ በሲኦል የነበሩን ነፍሳት ያወጣቸው ክቡር መስቀሉን በግሸን ደብረ ከርቤ ይቀመጥ ዘንድ ወደደ፡፡

አበው ግሸን ስለ ምን ተባለ ሲባሉ አባ ፈቃደ ክርስቶስ የቅድስት ድንግል ማርያምን ትዕዛዝ እና የታያቸውን ራዕይ ለማድረስ ስጋዊ ድካም ሳያጠቃቸው መጥተው በደረሱ ጊዜ ገስግሰን ደረስን አሉ፡፡ ይሄም ከዚያ መጣ ይላሉ፡፡ በዚህች የተቀደሰች ስፍራ አምላክ ስሙ ይመሰገንባታል፡፡ ክብሩም ይገለጥባታል፡፡

በዚህች ሥፍራ የነገሥታት ልጆች ጥበብ ስጋዊ እና ጥበብ መንፈሳዊን ተምረውባታል፡፡ የሀገር ፍቅር እና የሠንደቅን ክብርም መሠረት ይዘውባታል፡፡ የከበረች እና የጸናች ሃይማኖትንም አውቀውባታል፡፡

ዘመን አልፎ ዘመን ተተካ፡፡ አምላክ ዘመናትን አቀዳጀ፡፡ አጼ ዳዊት በኢትዮጵያ ምድር ነገሡ፡፡ እሳቸው በነገሡ ዘመን በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖች መከራና ስቃይ ይበዛባቸው ነበር፡፡ ሕዝብ የሚባርኩት ጳጳሳት ይታሠራሉ፣ ቀሳውስት ይገደላሉ፣ ምዕመናኑ ይሰየፋሉ፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ምዕመናን ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለዳዊት ይደርሱላቸው ዘንድ ተማጸኑ፡፡ ንጉሡ ዳዊትም ይሄን በሰሙ ጊዜ መኳንንቱን፣ መሳፍንቱን፣ ሊቃውንቱን እና የጦር አበጋዞችን ጉባኤ ጠሩ፡፡ በጉባኤውም የግብጽን ክርስቲያኖች ነጻ ያወጡ ዘንድ ተስማሙ፡፡ ለግብጹ ንጉሥም ጳጳሳቱን ይፈታቸው፣ ክርስቲያኖችንም በሰላም እንዲኖሩ ይተዋቸው ዘንድ መልእክት ላኩበት፣ ይህ ሳይኾን ቢቀር ግን ዓባይን ገድበው ግብጽን እንደሚቀጧት አስጠነቀቁት፡፡

ይህ በተሰማ ጊዜ በግብጽ ቤተ መንግሥት ዘንድ ሽብር ተፈጠረ፡፡ ንጉሡ ዳዊት ያሉትን ሁሉ ይፈጽሙ ዘንድ ተስማሙ፡፡ ለንጉሡ ዳዊትም የእጅ መንሻ ስጦታ ላኩ፡፡ ንጉሥ ዳዊት ግን ከስጦታዎች ሁሉ በእስክንድሪያ ያረፈው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ይልቅብኛል አሉ ይላሉ አበው፡፡ የግብጹ ንጉሥም ተጨነቀ፡፡ ግብጽ ያለ ዓባይ ከባሕር የወጣች አሳ ናትና ንጉሡ ያሉትን ያደርግ ዘንድ ግድ አለው፡፡ ከብዙ መከራ በኋላም ንጉሡ የፈለጉትን ፈቀዱ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የግብጽ ክርስቲያኖች ቁጥራቸው እየተመናመነ በመሄዱና መስቀሉን ይወስዱብናል ብለው በመስጋታቸው በሀገረ ኢትዮጵያ ይቀመጥ ሲሉ ለንጉሡ ዳዊት ሰጧቸው ይላሉ፡፡

ንጉሥ ዳዊትም መስቀሉን ተቀበሉ፡፡ ነገር ግን ሳይመለሱ በስናር አለፉ፡፡ በእርሳቸው መንበርም ጠቢብ የነበሩት ዘርዓያቆብ ነገሡ፡፡ ዘርዓያቆብም በነገሡ ጊዜ የአባታቸውን አደራ ያመጡ ዘንድ ወደ ስናር ገሰገሱ፡፡ አባታቸው ያላመጡትን መስቀልና ሌሎች የከበሩ ንዋየ ቅድሳትን ለማምጣት በአጀብ ሄዱ፡፡ በስናርም የከበረውን መስቀልና ሌሎች የተቀደሱ ንዋዬ ቅድሳትን ይዘው ተመለሱ፡፡

ንጉሡም መስቀሉን በተቀበሉ ጊዜ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር የሚል ራዕይ ተነገራቸው፡፡ ይሄንም ያደርጉ ዘንድ ተነሱ፡፡ በኢትዮጵያ አውራጃዎች መስቀለኛውን ተራራ ለማግኘት ተመላለሱ፡፡ የተፈቀደውን ተራራ ግን በቀላሉ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ መስቀለኛውን ቦታ ፍለጋ በተጓዙ ቁጥር መስቀሉ የኢትዮጵያን አውራጃዎች ሁሉ ይባርክና ይቀድስ ነበር፡፡ በየጊዜው መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አኑር የሚለው ራዕይ ደጋግሞ ይታያቸዋል፡፡ ንጉሡ ከአውራጃ ወደ አውራጃ እየተንከራተቱ መስቀለኛውን ሥፍራ ባጡ ጊዜ ሱባኤ ያዙ፡፡ በሱባኤውም አግዚአብሔር የግሸንን ተራራ አሳያቸው፡፡

ባሳያቸውም ጊዜ መስቀሉን አሸክመው፣ በፊት በኋላቸው፣ በግራ በቀኛቸው በብዙ ሠራዊት ታጅበው፣ ሕዝቡ እልል እያለላቸው በሆታም እያጀባቸው ወደ አምባሳል ገሰገሱ፡፡ በደረሱም ጊዜ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደኾነ አወቁ፡፡ በበዛ ሠራዊታቸው ታጅበው፣ መስቀሉን አሸክመው ተራራውን ዞሩት፡፡ ወደ ተራራውም ወጡ፡፡ መስቀሉንም በዚያች አስቀድማ በተመረጠች ሥፍራ አስቀመጡት፡፡

ንጉሡ የተቀበሉት መስቀሉን፣ ከለሜዳውን፣ ሐሞት ያጠጡበትን ሰፈነጉን፣ የተገረፈበት ጅራፉን፣ የተጎተተበት ገመዱን፣ አምስቱ ቀንዋትን ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፣ ሮዳስ የተባሉትን፣ አጽም አቅዱሳንን፣ በረከት ይኾናቸው ዘንድ የከበሩ ቅዱሳን መካናትን ነው፡፡ ይሄም ሁሉ በመስቀለኛዋ ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ አለ፡፡ መስቀሉ በግሸን አምባ ደርሶ ቅዳሴ ቤቱ በከበረ ጊዜ እግዘአብሔርም ከእናቱ ከማርያም እና ከእልፍ አእላፍ ቅዱሳን ጋር ተገለጠባት፣ ምድሪቱን ቀደሳት፣ ባረካት፣ የማይሻር ቃል ኪዳኑን ሰጣት፡፡

ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች አዲሱ ዓመት ጠብቶ በወረኃ መስከረም በ21ኛው ቀን ከምትከበረው ግሸን ማርያም በረከትና ረድዔት ለመካፈል ከየአቅጣጫው ወደ መስቀለኛዋ ተራራ ይገሰግሳሉ፤ መስቀሉና በመስቀሉ የተደረገላቸውን ሁሉ እያሰቡ እና እያመሰገኑ ይጓዛሉ፡፡ በመስቀለኛው ተራራም በአንድነት ይሰባሰባሉ፡፡ መስቀሉን ባሰቡት፣ ግሸንን ባስታወሷት ቁጥር አድካሚውን መንገድ ይረሱታል፤ በጽናት እና በእምነት ተራራውን ይወጡታል፡፡ እነኾ ያቺ ቀን ደርሳለች፡፡ ምዕመናን እናታችን እያሉ ወደ መስቀለኛው ተራራ ወጥተዋል፡፡ በመስቀለኛው ተራራ ከቅዱስ መስቀሉ መገኛ ከእናታቸው ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ከዳር ዳር መልተው ለጸሎት ቆመዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሳይበር ምህዳሩ የሚያሳያቸው ለውጦች ፈጣን እና ኢ-ተገማች ናቸው” የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ
Next article“የኢትየጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሽምግልና ሥርዓቶችን አካትቶ ቢሠራ ምክክሩን ውጤታማ ያደርገዋል” የታሪክ ምሁሩ አየለ በክሪ (ዶ.ር)