
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)“ሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ” ረቂቅ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የብሔራዊ ባንክ እና ሌሎችም መሰል የመንግሥት ተቋማት ተሳታፊ ኾነዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ የሳይበር ምህዳሩ የሚያሳያቸው ለውጦች ፈጣን እና ኢ – ተገማች መኾናቸውን ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲያችን የሳይበር ምህዳሩ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ እኩል የሚራመድ እና ለወቅቱ የሚመጥን እንዲኾን በማሰብ ረቂቅ ፖሊሲው መቀረጹን ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ ለማዘጋጀት ገፊ ከኾኑ ምክንያቶች መካከል ሳይበር ድንበር ተሻጋሪ ክስተት መኾኑ እና ባሕሪው ተለዋዋጭነት መኾኑ ነው ብለዋል።ሀገራችን እየተገበረችው ያለው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሳይበር ደህንነት በይበልጥ የሚፈልግ ጉዳይ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል። ከአየር ንብረት ቀጥሎ ትልቁ የዓለም ስጋት የሳይበር ጥቃት እንደኾነ እያየን ያለበት ኹኔታ ላይ መኾናችን እንዲሁም የሳይበር ዲፕሎማሲያችንን ማሳደግ እና የዲጂታል ሉአላዊነታችንን ለማስጠበቅ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲያችንን ወቅቱን ያመከለ አድረገን እንደንቀርፀው ትልቅ መነሻ ኾኖናል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ የሁሉም አካላት ኀላፊነት መኾኑን ገልጸዋል። ይህንንም ለማረጋገጥ ዜጎች፣ መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ማወቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ጉዳይ እና ኀላፊነት አድርጎ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የቴክኖሎጂ እድገትን እና የሳይበር ተለዋዋጭ ባህሪን ያማከለ እና ወቅቱን የሚመጥን ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ረቂቅ ማዘጋጀቱ ትልቅ እርምጃ መኾኑንም ሚኒስትር ድኤታው ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት የፖሊሲውን አስፈላጊነት ጠቅሰው ፖሊሲው ያሉበትን ክፍተቶች እና ሊይዛቸው ስለሚገባቸው ነጥቦች ከተቋማቸው ፍላጎት አንፃር የተለያዩ ሃሳቦችን እና ጥያቄዎችን አንስተዋል። ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!