“በትዝታ የተቀጣ፣ የሀገር ፍቅሩን ያልተወጣ- ልዑል”

38

ባሕርዳር፡ መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አባቱ ጠላት እንደ ቆሎ የሚጨበጥለት፣ ጦርነት እንደ ጨርቅ የሚጠቀለልለት፣ በየደረሰበት ሁሉ እጅ የሚነሳለት፣ በግርማውና በክንዱ ጦረኛ ሁሉ የሚበረግግለት ነው፡፡ መሳፍንት የከፋፈሏትን፣ መከራና ስቃዩዋን ያበዙባትን፣ ጀንበር በዘለቀች ቁጥር የሀገሬው እምባ የሚፈስስባትን፣ የዋይታና የሰቆቃ ድምጽ የሚሰማባትን፣ ጠላቶች በዙሪያ ገባው የከበቧትን፣ ክብሯንና ግርማዋን ለመድፈር የሚቋምጡላትን ሀገር አንድ ያደረገ ብርቱ ጀግና፡፡

በአማረና በተዋበ ፈረስ የሚገሰግስ፣ ለተጨነቀች ሀገር ፈጥኖ የሚደርስ፣ ዘመቻ ሄዶ ያለ ድል የማይመለስ፣ ከዘመን የቀደመ፣ ትናንት ላይ ቆሞ ነገና ከነገ ወዲያን ያለመ ባለ ራዕይ ነበር፡፡ ለሀገሩ ፍቅር፣ ለሠንደቁ ክብር ቃል ኪዳኑን በልቡ ውስጥ ያኖረ ቃል ኪዳን አክባሪም ነበር፡፡

የንጉሠ ነገሥት ልጅ ነው በግራና በቀኙ፣ በፊትና በኋላው አጀብ የሚበዛለት፣ ፀሐይ እንዳይመታው የሚከለልለት፣ በጎዳናዎች በወጣ ጊዜ የተሸለመ ሰረገላ የሚቀርብለት፣ እንደ ዓይን ጥቅሻና እንደ ከንፈር ንክሻ የፈጠኑ ጀግኖች የሚያጅቡት፣ ታላላቆቹ ባዩት ጊዜ ምርቃት የሚያወርዱለት፣ ታናናሾቹም በተመለከቱት ጊዜ እንደ እርሱ ባደረገን እያሉ የሚቀኑበት ልዑል ነበር፡፡

የአባቱን ዙፋን ይቀባ ዘንድ ተሰፋ የተጣለበት፣ እንደአባቱ ሁሉ ጀግናና ሀገሩን አፍቃሪ፣ ሀገሩንም በጀግንነት መሪ እንደሚኾን የተነገረለት ልዑል የተባለው ሳይደርስለት፣ የታለመው ሳይሰምርለት ሁሉም እንደ ጉም ተበትኖበት፣ እንደ ጭስ ተኖበት ቀረ፡፡

ያ ቃል ኪዳኑን ከሹርባው ጋር ያሠረ፣ የሚመጣውን ዘመን አስቀድሞ የመረመረ ኀያል ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ ልዑሉ በተወለደ ዘመን የነበረው ደስታ እጹብ ነበር ይባላል፡፡ ልዑሉ በተወለደ ጊዜ እልልታው ከዳር እስከ ዳር አስተጋብቷል፣ ቤተ መንግሥቱ በእልልታና በሆታ ድምጽ ከዳር ዳር ተናግቷል፣ ደስታው እጥፍ ድርብ የነበረውን ቴዎድሮስ አዳራሹን አሳምሮ ግብር አብልቷል፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ ካህናቱ፣ የጦር አበጋዞች እና የእልፍኝ አስከልካዮች ሁሉም በንጉሡ ደስታ ደስ ተሰኝተዋል፤ ለንጉሡ እና ለእቴጌይቱም እጅ እየነሱ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

ንጉሡን ዓለም ያሳየው ልጅ ነበርና ዓለማየሁ ተባለ፡፡ አባቱ ዓይቶ የማይጠግበው፣ ስሞ የማይሰለቸው፣ ታቅፎት ውሎ ታቅፎት ቢያድር የማይደክመው፣ ባየውና የልጅነት ፍቅሩን በሰጠው ጊዜ ከኀይል ላይ ኀይል ከጉልበት ላይ ጉልበት የሚሰማው፣ ከዓይኑ በራቀ ጊዜ እጅግ የሚናፍቀው የደስታ ምንጭ የኾነ ልዑል ነበር፡፡ መኳንንቱ ባገኙት ቁጥር በደስታ የሚስሙት፣ ጀግኖች የጦር መሪዎች በስስት የሚመለከቱት፣ በናፍቆት የሚያዩትን ተወዳጅ ልዑል፡፡

ዳሩ ምን ያደርጋል ዘመንን የቀደመው፣ ራዕይ አላስተኛው ያለው አባቱ በመቅደላ አናት ላይ ከተራራው የገዘፈ ታሪክ ሠርቶ፣ ከቋጥኝ የላቀ ስም ትቶ ሲያልፍ ልዑሉም ሁሉም ቀረበት፤ ዓይቶ የማይጠግበው አባቱን፣ ጡት አጥብታ ያሳደገችው እናቱን፣ በፊትና በኋላው የሚበዛለትን አጀቡን፣ ደስታና ድሎቱን፣ በመኳንንትና በመሳፍንት መታጀቡን፣ እንደ አንበሳ በጀገኑ፣ እንደ ነብር በፈጠኑ የጦር አበጋዞች መከበቡን ሁሉንም አጣው፡፡ ሁሉንም መቅደላ ዘጋው፡፡ የአባቱ መሞት ከአንጀቱ ሳይወጣለት፣ በሚያማምሩ የልጅነት ጉንጮቹ የሚፈስሰው እንባው ሳይደርቅለት እናቱም አባቱ ወደሄደበት ዓለም ተከተለችና ሀዘኑ እጅግ የመረረ ኾነበት፡፡

በደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረ ሃና ባሕል ጥናት ዳይሬክተር እና የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ የአጼ ቴዎድሮስ የሕይወት መዝገብ ሲገለጥ የልዑል ዓለማየሁ ታሪክም አብሮ ይገለጣል፤ የልዑል ዓለማየሁ እትብት ማረፊያ ደብረ ታቦርም ትነሳለች ይላሉ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ልዑሉ በተወለደ ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኝተዋል፤ ቀጣዩ የመንበረ ሥልጣናቸው ወራሽ፣ የእርሳቸውን ራዕይና ተስፋ አስቀጣይ የኾነ ልጅ አግኝተዋልና፡፡

ልዑል ዓለማየሁ መወለዱ እንዳስደሰተ ሁሉ ፍጻሜው ግን ያማረ አልነበረም፡፡ ልዑሉ በለጋ እድሜው፣ በአልጠና ልቡናው የአባትና የእናቱን ሞት በዓይኑ አይቷል፤ አባቱ የሀገር ፍቅር አንገብግቦት ስለ ሀገር ክብር ራሱን መስዋዕት ሲያደርግ ተመልክቷል፤ ይህ እንደ አሳዘነው ይሄም እንዳስተከዘው የኖረ ልዑል ነው የሚሉት መምህሩ፡፡ ተክለጻዲቅ መኩሪያ አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው ከመቅደላው ፍጻሜ በኋላ ስለነበረው ሲጽፉ እቴጌ ጥሩወርቅ ከመቅደላ ወርደው ከእንግሊዞች ጋር ወደ ስሜን እየሄዱ በመንገድ እንዳሉ አርፈዋል ብለዋል፡፡ ልዑሉ የእናትና የአባት መከራን ያዬ መከረኛ ኾነ፡፡

ልዑል ዓለማየሁ እናትና አባቱን አጥቶ እኒያ ጀግና ጦረኞች እና የቴዎድሮስ የቁርጥ ቀን ታማኞች ስለ ሀገር ወድቀው ብቻውን ቀረ፡፡

ቴዎድሮስ ስለ ክብር ራሳቸውን ሲሰዉ የአንግሊዝ ጦር በመቅደላ የነበረውን ሃብት ዘረፈው፣ አወደመው፡፡ የሚችለውን ወደ ሀገሩ ይዞ ሄደ፤ የማይችለውን አውድሞት ከመቅደላ አምባ ወረደ፡፡ የእንግሊዝ ጦር ወደ ሀገሩ ሲመለስ ልዑል ዓለማየሁም ወደ እንግሊዝ እንዲሄድ ተደረገ፡፡ እንደ ታሪክ መምህሩ ገለጻ እቴጌ ጥሩወርቅ ለእግሊዛዊ ካፒቴን ስፒዲ( ባሻ ፈለቀ) አደራ ሰጥተዋለች፡፡ እቴጌ ጥሩ ወርቅ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥታ ካፒቴን ስፒዲን ( ባሻ ፈለቀ) አስምላ ነበር ልጇን አደራ ያለችው፡፡ ኢትዮጵያውያን ባሻ ፈለቀ የሚሉት ካፒቴን ስፒዲ በጋፋት አማርኛ ቋንቋን የተማረ ነበርና ለልዑል ዓለማየሁ ሞግዚት እንዲኾን የተፈለገው እርሱ ነበር፡፡

እቴጌ ጥሩወርቅ ልጃቸው ቀጣዩ አልጋ ወራሽ ይኾናል ተብሎ ስለሚሰጋ ዙፋኑን የሚመኙ እንዳይገድሉባቸው ነበር ይሄን አደራ የሰጡት ይላሉ መምህሩ፡፡ ይሄን አደራ እንደሰጡ እሳቸው አለፉ፡፡ ልዑል ዓለማየሁም ከባዕዳን ጋር ባሕር ተሻግሮ ወደ እንግሊዝ ገሰገሰ፡፡ ልዑሉ የሚመስሉትን ሁሉ በሀገሩ ጥሎ፣ ባዕዳንን ተከትሎ የሄደ ነበርና ብቸኝነት ያንገበግበው ጀመር፡፡

ፍሊፕ ማርስዲን በጻፉትና በብሩክ መኮንን የቴዎደሮስ ዕዳ አንዲት ኢትዮጵያ ተብሎ በተተረጎመው መጽሐፍ “ ሕጻኑ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ በ1868 በበጋ መጀመሪያ ላይ ለንደን ፕላይማወዝ ደረሰ፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያም ለሕጻኑ ልዩ ፍቅርና እንክብካቤ ለገሡት፡፡ በእርሳቸው ሞግዚትነትና ቅርብ ክትትል ስር ከሚያድጉት ከዴልፒ ሲንግ እና ከሕንድ ልዑላን ኾነው ከተላኩ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ልጆች ጋር እንዲኖር ማድረግም አስበው ነበር፡፡ የሚያሳዝነው እና ባይተዋሩ የሐበሻው ልዑል ከካፒቴን ስፒዲ ጋር የመሠረተውን ቅርርብ የወላጅና የልጅ ትስስር ያህል መሆኑን ስለተገነዘቡ ለሕጻኑ ዘላቂ ሕይወት ከታሰበ በፍጹም ከእርሱ ሊነጠል አይገባውም ብለው ተውት” ተብሏል፡፡

የእቴጌ ጥሩወርቅ እናት የልዑል ዓለማየሁ አያት ወይዘሮ ላቂያዬ ስለ ልጃቸው ደኅንነት እና እንክብካቤ ደብዳቤ እየጻፉ አደራ ይሉ ነበር፡፡ ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤም “ የቀረኝ ደጅ አዝማች ዓለማየሁ ነው፡፡ አደራዎን ይጠብቁልኝ፡፡ እግዚአብሔር አባቱን እና እናቱን ቢነሳው እርስዎን ሰጥቶታል፡፡ እኔም ካላየሁት ከሞቱት ቁጥር ነኝ፡፡ እርስዎን እናቴ ይላል እንጂ እኔን እናቴ አይለኝም፡፡ አላሳደግሁትምና፡፡ እርስዎ ያሳድጉት ስለ እግዚአብሔር ብለው” ማለታቸውን ተክለጻዲቅ መኩሪያ ጽፈዋል፡፡ ይህም ያደራ ቃል ንግሥት ቪክቶሪያ የበለጠ እንዲንከባከቡት አድርጓቸዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ መስከረም 21/2016 ዓ.ም ዕትም
Next article“የሳይበር ምህዳሩ የሚያሳያቸው ለውጦች ፈጣን እና ኢ-ተገማች ናቸው” የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ