
ባሕርዳር፡ መስከረም 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማራኪው የወሎ መልካ ምድራዊ አቀማመጥ ላይ ደርባባዋ ግሸን ደብረ ከርቤ ተጨምራበት ተፈጥሮን ከመንፈሳዊነት ጋር አንሰላስለው እስከ ሰማየ ሰማያት ያስተጋቡታል፡፡ መስከረም ሲጠባ፤ አደይ አበባ ሲፈነዳ በበርካቶች ዘንድ በምዕናብ ውል ውል ከሚሉት አካባቢዎች አንዱ ወሎ ነው፡፡
“ውል ውል አለኝ ደጅሽ” የሚባልላት የአምባዋ ላይ እመቤት ግሽን ደብረ ከርቤ ሁልጊዜም በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን በተለየ መልኩ ትነግሳለች፡፡
ወሎ ድንበር አልባ የፍቅር ተምሳሌት ነው፡፡ ወሎየነት ተወዳጅ የሕይዎት ጣዕምና ለዛ ነው፡፡ ወሎንም ወሎየነትንም አይቶ ለመረዳት እድል ከሚሰጡት መልካም አጋጣሚዎች መካከል የአምባዋ ላይ እመቤት የምትነግስበት መስከረም 21 አንዱ ነው፡፡ ከዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ ንግሥና ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ግማደ መስቀሉን ሊሳለሙ፤ የጌታን እናት ሊማጸኑ በየዓመቱ በዚህ ወቅት ወደ ግሸን አምባ ያቀናሉ፡፡
እንደ ዛሬው የትራንስፖርት አማራጮች ሳይሰፉ ጥንት ኢትዮጵያዊያን አድካሚውን የእግር ጉዞ በብርታት፤ ፈታኙን የአምባ ላይ ጉዞ በጽናት አጠናቅቀው ከአምባው ጫፍ ላይ ሲደርሱ ሃሴታቸው ምድራዊ ብቻ ሳይኾን ሰማያዊ በረከትም አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ የሚረግጧት ምድር የክርስቶስ ግማደ መስቀል በክብር ያረፈባት እና የተመረጠች መስቀለኛ ቦታ ናት፡፡ ይህንን ክብር የግብጿ አሌክሳንድሪያ ተመኝታው አልተሳካላትም፤ ፋርስም ይህ እንዲኾንላት ፈልጋ አልቻለችም ነበር፡፡
በሐይቅ እና መቅደላ፤ በደላንታ እና በየጁ መካከል የምትገኘው የግሸን አምባ የበሽሎ ወንዝ አዋሳኟ ነው፡፡ የአምባሰል ሰንሰለታማ ተራሮች ለክብሯ ዘብ የቆሙላት ግሸን የበሽሎ ወንዝ ዘመናትን እንደ ጅረት የፈሰሰው ውበቷ የሚቀዳበት ወንዝ ነው፡፡ ተለያየን ወደ ግሸን የሚያቀኑ ምዕመናን ከድካማቸው አርፈው፤ ላበታቸውን አለቃልቀው ፋታ የሚያገኙበት የአካባቢው ጸጋ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ክርስቲያኖች የክርስቶስን ግማደ መስቀል ለመሳለም እና ለመጎብኘት ዘወትር በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ይተምማሉ፡፡ ምድሯን የረገጠ ሁሉ ምህረትን፤ ደጇን የጎበኘ ሁሉ ድኅነትን ያገኝባታል የሚባልላት የተራራዋ ላይ እመቤት እንደ ዘንዶ በተጥመለመለው መልካ ምድራዊ አቀማመጧ መውጫዋም ኾነ መውረጃዋ መንገድ አንድ ብቻ ነው፡፡ በዚያች ቀጭን የንስሃ መንገድ እልፎች ወደ ላይ ዘልቀው እልፎች ወደታች ሲመለሱ እክል እንኳን አይገጥማቸውም፡፡
በዚያም ዘመን ቤተ ክህነቱን ከሚመሩት ኢትዮጵያዊያን ጳጳሳት ከአባ ሚካኤል እና ከአባ ገብርኤል ጋር ሀገረ መንግሥቱን የሚመሩት ንጉሠ ነገሥቱ ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ በዚች ቅድስት የተራራ ላይ አምባ ሱባዔ ገቡ፡፡ በሱባያቸው መጨረሻም “ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን እየሩሳሌምን ትኹን፤ ይህች ቦታ የተሰቀልኩባትንም ቀራኒዮንም ትሁን፤ የተቀበርኩባትንም ጎለጎታን ትሁን” የሚል ቃል ኪዳን ተገባላቸው ይላሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፡፡
“እንኳን ሰው የሰገረ ቆቅ፤ የበረረ ወፍ እንኳን እንዳይገደልባት ዳሯ እሳት መሃሏ ገነት” ትኹን ስለመባሏ የቦታዋን እና የንዋየ ቅዱሳቷን ታሪክ በያዘው “መጽሐፈ ጤፋት” ተቀምጧል ይባላል፡፡ የተራራዋ ላይ ብርሃን ስለዓለም ሰላም፤ ስለኢትዮጵያም ደኅንነት ቀን ከሌሊት ምኅረት ይለመንባታል፤ ሰላም ይሰበክባታል፡፡ አባቶች ዘወትር በፀሎት “የአስራት ሀገርሽን ጠብቂ” እንደሚሉ ሁሉ ምዕመኖቿም ዛሬ ስለሕይዎታቸው ምኅረት፤ ስለሀገራቸው ደኅንነት በተራራዋ ላይ አምባ ይሰባሰባሉ፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!