
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደንቢ ሐይቅና ፏፏቴን የገበታ ለትውልድ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የደንቢ ሐይቅና ፏፏቴ እንዲሁም አስደማሚው ዕድሜ ጠገብ የተፈጥሮ ደንና ቡና እርሻ የገበታ ለትውልድ ቱሪዝም ማዕከል እንዲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ነጋሽ ወጌሾ ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለጹት የደንቢ ሐይቅ ሎጅና ተያያዥ መሰረተ ልማት ስራዎች ሲጠናቀቁ ለሚዛን አማንና አካባቢው ተጨማሪ የቱሪስት ስበት ማዕከል በመሆን የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ ይሆናል:: ኢዜአ እንደዘገበው አያይዘውም ብልጽግና በየአካባቢው የሚገኙትን ፀጋዎች በመለየት ከምናባዊ እይታ ወደ ገቢራዊ ልማት በመቀየር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለመታከት ይሠራል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!