“የተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መኾን መሠረት ይጥላሉ።” አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

54

ባሕር ዳር: መስከረም 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተፈጥሮ ጸጋዎችን ከሰው ኃይል ጋር በማስተሳሰር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መኾን መሠረት የሚጥሉ መኾናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጅማ እና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸውም በዋናነት በአካባቢዎቹ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት፣ እንዲሁም የግብርና ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በጅማ ከተማ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት የሚከናወነው የቱሪዝም ልማት ሥራም የጉብኝቱ አካል ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ በጉብኝታቸው በጅማ ዞን ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው በቡና፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቱሪዝም ልማት አበረታች ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም ጠቁመዋል፡፡ይህም የፌደራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎች በውጤታማ መንገድ ላይ መኾናቸውን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ መሰል የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አፈ- ጉባኤው አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በርካታ ፈተናዎችን በጋራ በማለፍ አብሮነታቸውን አስጠብቀው መቀጠላቸውንም ነው የተናገሩት። ይህንን የሕዝብ አብሮነትም በልማት ሥራዎች በማስተሳሰር ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ አኳያ በሌማት ትሩፋትና ቱሪዝም ልማት የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ በጉብኝታቸው በጅማ ከተማና አካባቢው በርካታ አዳዲስ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም ከዚህ ቀደም በአካባቢው የማይመረቱ እንደ ሩዝ ያሉ ምርቶችን በስፋት ማልማት ተችሏል ብለዋል። የቡና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ረገድም ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በጅማ ከተማ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ አቅም እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው በሌማት ትሩፋትና ግብርና ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በማሳለጥ ረገድ ሚናቸው የጎላ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አኳያ አመራሩ በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በሁሉም አካባቢዎች በማስቀጠል ረገድ ይበልጥ መሥራት እንዳለበትም አቶ አባ ዱላ ገመዳ ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለተማሪዎች ድጋፍ ተደርጓል” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደንቢ ሐይቅና ፏፏቴን የገበታ ለትውልድ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።