
ደሴ: መስከረም 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 64 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ማከናወኑን የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል። ለክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተለይተው ከታቀዱ ወጣቶች 75 በመቶ መሳተፋቸውንም መምሪያው ገልጿል።
የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጀማል ሞላ እንዳሉት በዞኑ የክረምት ወራት በ13 ዋና ዋና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ ከታቀደው 583 ሺህ ወጣቶች መካከል የእቅዱን 75 በመቶ ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 205 አዳዲስ ቤቶች ተገንብተዋል ያሉት ኅላፊው ለ134 ቤቶች ደግሞ የጥገና ሥራ በመሥራት ለአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ማስተላለፍ ተችሏል ነው ያሉት።
ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 12 ሺህ ደርዘን ደብተር እና ከ1 ሺህ በላይ ፓኮ እስክብሪቶ ከተለያዩ ተቋማት እና ባለሃብቶች በማሰባሰብ 15 ሺህ የሚኾኑ ተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ከ119 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በዞኑ መትከል ተችሏል ያሉት አቶ ጀማል 531 ዩኒት ደም ማሰባሰብ ተችሏልም ብለዋል። የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ የከተማ ውበትና ጽዳት፣ የመንገድ ጥገና፣ በወንጀል መከላከል እና የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ላይ ተኩረት ተደርጎ መሠራቱንም ኅላፊው ገልጸዋል። በበዓላት ወቅት አቅመ ደካሞችን እና አረጋዊያንን ማዕድ የማጋራት ሥራ መሥራት ተችሏል ያሉት አቶ ጀማል በመንግሥት ይሸፈን ቢባል ሊወጣ የሚችለውን 64 ሚሊዮን ብር ሃብት ማዳን ተችሏል ነው ያሉት።
በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብርም የአረጋውያንን ቤት መገንባት፣ የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ እና የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ትኩረት ከሚደረግባቸው ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል። በዞኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ኀላፊው በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይም በክረምቱ የታየውን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!