“አንድነትን የሚሸረሽሩ፣ ልዩነትን የሚያሰፉ እና ሰላምን የሚያውኩ አስተሳሰቦችን አምርሮ መታገል ያስፈልጋል።” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

154

ባሕር ዳር: መስከረም 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የሰላም ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡ የምክክር መደረኩ በክልሉ ወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ያለመ ነው ተብሏል።

የዋግ ሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎቹን በሠለጠነ መንገድ በማቅረብ የሚታወቅ ሕዝብ ነው ያሉት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ሕዝቡ የሚጠይቃቸውን የልማት እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች ከመንግሥት መጠበቅ ብቻ ሳይኾን በራሱ ተሳትፎ ጭምር የሚሠራ ሕዝብ ነው ብለዋል።

የዋግ ሕዝብ የሰከነ፣ የተረጋጋ እና በፈተና ወቅትም ችግርን በጥበብ መሻገር የሚችል ሕዝብ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በአካባቢው የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለማስቆም የቀደመ ልምዱን፣ ጥበቡን እና የአባቶቹን ውርስ ማስቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችም ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ክልላዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ፣ ልዩነትን የሚያሰፉ እና ሰላምን የሚያውኩ አስተሳሰቦችን አምርሮ መታገል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የክልሉን እና የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥም ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ተቀራርቦ እንዲሠራ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ጠይቀዋል፡፡

ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በምክክር መድረኩ ከወረዳዎች እና ከከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ወጣቶች፣ የምሥራቅ ዕዝ ከፍተኛ መሪዎች፣ የዞን እና የክልል የሥራ ኅላፋች ተሳታፊዎች ናቸው።

በምክክር መድረኩ ከምክጽል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በተጨማሪ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ፍሰሃ ደሳለኝ እና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ኮሎኔል ጠይቅ ዘመነ ተገኝተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጣና ሞገዶቹ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ።
Next articleከ64 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ማከናወኑን የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ፡፡