
ደሴ፡ መስከረም 19/2016 (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሕዝባዊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በደሴ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሰ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የተገኙት በሰሜን ምሥራቅ ዕዝ የ801ኛ ኮር የተወርዋሪ ሻለቃ አዛዥ፣ የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አባል ሻለቃ ደገሰው ዶሻ “ሰራዊቱ ከደመወዙ ቀንሶ ለወገኖቹ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።
ሻለቃ አዛዡ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የሕዝብ እና የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅ ከሚከፍለው ዋጋ ባለፈ ለአቅመ ደካማ ወገኖቹ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠልዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በደሴ ከተማ አስተዳደር 60 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማበርከቱን የጠቀሱት ሻለቃ ደግሰው ቀደም ሲልም በደቡብ ወሎ ዞን ከ150 ለሚበልጡ ተማሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ሰላም ለማስፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሻለቃ ደግሰው አሳስበዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ባደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደሰታቸውን የተማሪ ወላጆች እና ተማሪዎቹ ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!