“በጎዳና ሕይወት ውስጥ የሚኖሩ ሕጻናትን መታደግ ትውልድን ማዳን ነው” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር

32

ደብረ ብርሃን: መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ ከተሞች ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሕጻናት የኋላ ታሪካቸውን ለጠየቀ የሚያገኘው ምላሽ ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች፣ ወላጆቻቸውን በሞት ማጣትና ሌሎች ተያያዥ ፈተናዎች ይኾናል።

ታዳጊዎቹ ህይወታቸውን ጎዳና ላይ ሲያደርጉ ለሥነ ልቦናና ለዘርፈ ብዙ የጤና ቀውሶች ይዳረጋሉ፡፡

በእንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከመሠረት በጎ አደርጎት ድርጅት ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡

በጎ አድራጎት ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ 43 ሕጻናትን ለሦስት ወራት ያህል የምግብ፣ የአልባሳት ፣ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እና ዘላቂ የሥነ ልቦና ምክር በማዘጋጀት ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ ስልጠና ሰጥቶ ዛሬ አስመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አሚኮ ያነጋገራቸው ታዳጊዎች በዝቅተኛ የምጣኔ ሃብታዊ ደረጃ መገኘታቸው፤ በተለያየ ምክንያት ከወላጆቻቸው በመለየታቸው በሱስ ለመጠመድ እና ሕይወታቸውን ጎዳና ላይ ለማሳለፍ እንደተገደዱ ነው የሚናገሩት፡፡

ለወራት በቆዩበት ጊዜ ያገኙትን የሥነ ልቦና ምክርና ዕውቀት በሥራ ላይ አንደሚያውሉት የተናገሩት ታዳጊዎቹ እንደ ጎዳና ላይ ሕይወት አስከፊ ነገር የለም ነው ያሉት፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች ሕጻናትና ማኅራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ በለጥሽ ግርማ ሕይወታቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ 110 ጎልማሶችንና 143 ሕጻናትን በተመሳሴይ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡
የአልባሳት ፣ የሕክምና ፣ የምግብና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል 17 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ነው ኀላፊዋ የተናገሩት፡፡

ሕጻናቱ እና ጎልማሶቹ በድርጅቶቹ የነበራቸውን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ ለ15 ወራት ያህል ክትትል እንደሚደረግላቸውም አብራርተዋል። ማኅበረሰቡም ትውልድን ለመታደግ ለሕጻናት ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመጀመሪያው የዓለም የጎዳና ላይ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነገ በላቲቪያ ሪጋ ይካሄዳል
Next article“ሰራዊቱ ከደመወዙ ቀንሶ ለወገኖቹ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል” ሻለቃ ደግሰው ዶሻ