የመጀመሪያው የዓለም የጎዳና ላይ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነገ በላቲቪያ ሪጋ ይካሄዳል

47

ባሕርዳር፡ መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም አትሌቲክስ ከቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮና ማግስት ፊቱን ወደ ዓለም የጎዳና ላይ ውድድር መልሷል። በላቲቪያ ሪጋ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ውድድሮች ቻምፒዮ ነገ ይካሄዳል። ውድድሩ በ9 ርቀቶች ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በውድድር መድረኩ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ አትሌቶች ይፎካከራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያን የሚወክለው ብሔራዊ ቡድን የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

በውድድሩ ከ57 ሀገራት የተወጣጡ 347 አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን በ9 ርቀቶች ውድድሩ ይካሄዳል ተብሏል።

ከዓለም ቻምፒዮና እና ከዳይመንድ ሊግ መልስም በጎዳና ውድድሮች ስኬታማ የነበሩ አትሌቶች ወደ ስፍራው አቅንተዋል።

13 አትሌቶችን የያዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልዑክም ትናንት ምሽት ሽኝት ተደርጎለታል። ሰባት ሴት እና ስድስት ወንድ አትሌቶች ያካተተው ልዑኩ በ1 ማይል፣ በ5 ኪሎ ሜትር እና ግማሽ ማራቶን በሴቶችም በወንዶችም ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ልዑኩ ስኬታማ ውድድር በማድረግ ሀገሩን በድጋሚ እንደሚያኮራ ያላትን እምነት ገልጻለች ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ይጀመራል።
Next article“በጎዳና ሕይወት ውስጥ የሚኖሩ ሕጻናትን መታደግ ትውልድን ማዳን ነው” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር