በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሸገር ደርቢ ይጠበቃል፡፡

167

11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ፤ የሸገር ደርቢ  ደግሞ ትኩረት ስቧል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ደርቢ እንደሆነ የሚነገርለት የሸገር ደርቢ ዛሬ ጥር 20/ 2012 ዓ.ም ይደረጋል፡፡ በአስደናቂ የአደጋገፍ ስርዓትና በከፍተኛ የሜዳ ላይ ፉክክር የሚታወቁት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁልጊዜም በጉጉት ይጠበቃል፡፡

ዛሬ ከቀኑ 10፡00 የሚደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በ11ኛ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ትልቅ ግምት የተሰጠው ነው፡፡ በቀድሞ ተጫዋቻቸው ካሳዬ አራጌ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሜዳ ላይ እያሳዩት ያለው የአጨዋዎት ስርዓት ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ኳስን በራስ ሜዳ በመመሥረት እና ተቃራኒ ቡድንን በኳስ ቁጥጥር በመብለጥ የሚጫወቱት ቡናዎች በሸገር ደርቢም የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

ታላላቅ ተጫዋቾችን በማስኮብለል የሚታወቁት የሰርዳን ዝቪጂኖቭ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ መልሶ በማጥቃትና ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ለቡናዎች ፈተና እንደሚሆኑባቸው ይጠበቃል፡፡ ቡድኖቹ በሸገር ደርቢ እስካሁን ድረስ በሊግ ጨዋታ 40 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም 18ቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ40 የሊግ ግንኙነታቸው 6 ጨዋታዎችን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻሉት፡፡ በቀሪዎቹ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በተገናኙባቸው የሊግ ጨዋታዎች ቅዱሰ ጊዮርጊስ 49 ግቦችን በኢትዮጵያ ቡና መረብ ላይ በማሳረፍ ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንጻሩ 24 ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ወቅታዊ አቋማቸው መልካም የሚባል በመሆኑ የዛሬውን ጨዋታ የበለጠ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ17 ነጥብና በሦስት ንጹህ ግብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንጻሩ በ13 ነጥብና በስድስት ንጹህ ግብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

የ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ከአንድ ጨዋታ በስተቀር ዛሬ ሲደረጉ ባሕር ዳር ከነማ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታል፡፡ ፋሲል ከነማ ደግሞ ወደ ጅማ አቅንቶ ከጅማ አባጅፋር ጋር ይጫወታል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ከሰበታ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ፣ ሐዋሳ ከተማ ከወላይታ ዲቻ፣ መቀሌ 70 እንደርታ ከስሑል ሽረ ጋር ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታዎቹ 9፡00 ይደረጋሉ፡፡ የ11ኛ ሳምንት  አንድ ጨዋታ ነገ ሲቀጥል ሲዳማ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ይጫወታሉ፡፡

ፕሪሚዬር ሊጉን የአምናው አሸናፊ መቀሌ 70 እንደርታ በ19 ነጥብና በ4 ንጹህ ግብ ይመራዋል፡፡ ፋሲል ከነማ ደግሞ በ18 ነጥብና በ10 ንጹህ ግብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ወልቂጤ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማና ሀድያ ሆሳዕና በወራጅ ቀጠናው ይገኛሉ፡፡

በታርቆ ክንዴ

Previous article‹‹ፍትህ ለታገቱ ተማሪዎች፡፡›› የዋሽንግተን ዲሲ ሠላማዊ ሰልፈኞች
Next articleቻይና 1 ሽህ አልጋዎች ያሉት ሆስፒታል በ48 ሰዓታት ገንብታ ሥራ አስጀመረች፡፡