
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡ በዓመታዊ የንግስ በዓሉ ላይ 1 ሚሊን የሚጠጉ ምዕመናን እና ጎብኝዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ንግሥ ለረጂም ዘመናት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝበ ክርስቲያን በተገኘበት ይከበራል። በተራራዋ አምባ ላይ ዘወትር በየዓመቱ መስከረም 21 የሚውለውን ንግስ በርካቶች በጉጉት እና በናፍቆት ይጠብቁታል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ መስፍን መኮንን በክልሉ ከሚከበሩ ደማቅ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ንግስ አንዱ እና ተጠባቂው ነው ብለዋል፡፡ የግሸን አምባ የግማደ መስቀሉ ማረፊያ ከመኾኗ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ መስከረም 21 ድረስ በዓሉ በድምቀት ይከበራል ነው ያሉት፡፡
በ2016 ዓ.ም ከመስከረም 14/2016 ዓ.ም ጀምሮ አካባቢውን ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት ኅላፊው ከመስከረም 15/2016 ዓ.ም ጀምሮም ጎብኝዎች ወደ አካባቢው በመግባት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የመስቀል በዓል ሰላማዊ በኾነ መንገድ መከበሩን ያነሱት ኅላፊው “ለግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” ብለዋል፡፡ የጤና፣ የውኃ እና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ ነው ያሉት ኅላፊው አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
አቶ መስፍን በዓሉ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በአካባው የሚገኘው ኮማንድ ፖስትም ሙሉ ኅላፊነት ወስዶ የጸጥታ ሥራውን እየሠራ መኾኑን ያነሱት መምሪያ ኅላፊው ገብኝዎች ያለምንም ስጋት በግሸን ደብረ ከርቤ ተገኝተው ዓመታዊ የንግስ በዓሉን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓሉ ለአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጨማራ ምጣኔ ሃታዊ ተጠቃሚነትን የሚፈጥር በመኾኑ ማኅበረሰቡ የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል ሊያሳይ ይገባል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በኮሮና ወረርሽኝ እና ተደጋጋሚ ጦርነት የጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱን መምሪያ ኅላፊው ጠቁመዋል፡፡ ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ጎብኝ እና ምዕመን በበዓሉ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዓመትም 1 ሚሊዮን የሚጠጋ የበዓሉ ተካፋይ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!