
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሻሸ እና ጓደኞቿ የበጎ አድራጎት ማኅበር “አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ከትምህርት ገበታው እንዳይለይ” በሚል ሃሳብ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የሻሸ እና ጓደኞቿ የበጎ አድራጎት ማኅበር አስተባባሪ ሻሸ አስካለማርያም ድጋፉን ለ8ኛ ጊዜ እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ለ2 መቶ ተማሪዎች የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ እና ደብተር ድጋፍ መደረጉን የጠቆሙት አስተባባሪዋ ድጋፉ ተማሪዎች በመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማገዝ ያለመ እንደኾነ አንስተዋል።
ድጋፉን ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ እና ሰማይ ፈርኒቸር የተበረከተላቸው መኾኑንም ተናግረዋል። በጎ አድራጎት ማኅበሩ ከድጋፉ ባሻገር ተማሪዎችን በቋሚነት የሚያስተምሩ በጎ አድራጊዎችን እየፈለገ ልጆችን ከአሳዳጊዎች እያገናኘ መኾኑንም ጠቁመዋል። አስተባባሪዋ በቀጣይ የተሻለ ድጋፍ ሰጪ በማፈላለግ ተማሪዎችን በቋሚነት ለማገዝ እቅድ እንዳላቸውም አንስተዋል።
ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቅለው በባሕር ዳር ከተማ የተጠለሉት አቶ አዱኛ አበበ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ቀድሞ የተሻለ ኑሮ ይመሩ እንደነበረ ገልጸው አኹን በተደረገላቸው ድጋፍ የልጆቻቸው ትምህርት እንደማይቋረጥ ተናግረዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች ድጋፍ የቤተሰቦቻቸውን ጭንቀት እንዳቃለላቸው ተናግረዋል።
የተሠጠነው የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ እና ደብተር መጀመሪያ ትምህርት ቤት ለመግባት ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው ያሉት ተማሪዎቹ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት።
ለስምንተኛ ጊዜ የተደረገው ድጋፉ ከ4 መቶ ሺህ ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!